
“የአሸባሪው ትህነግ በደልና ሴራ የአማራን ሥነልቦና አጠነከረው እንጂ አላዳከመውም”
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ ጽንሰቱም፣ ውልደቱም፣ እድገቱም ኾነ ተግባሩ ሀገር በማፍረስ ዓላማ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሀገርን የመዝረፍ፣ ሕዝብን የመከፋፈልና ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈጸም የጀመረው ከውልደቱ ጀምሮ ነው፡፡
የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሙ የአማራ ሕዝብን በጠላትነት በመፈረጅ የተዘጋጀ ነው፤ በዚህም በተለዬ መልኩ በአማራ ሕዝብ ላይ በደል አድርሷል፤ በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ሊፈጸሙ የማይገባቸውን ግፎች እየፈጸመ ዓመታትን አሳልፏል። በተለይ የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎና ጥያቄ በነበራቸው ሰዎች ላይ አፈና፣ ግድያ፣ እስራት፣ ስቃይ፣ ማፈናቀልና ሌሎች ግፎችም ተፈጽመዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ አርሶ የሚመግብ የሕዝብ አለኝታ፣ ሀገርና ወገን በተደፈረ ጊዜ ደግሞ ግዳጅ የሚሰለፍ መከታ ነው፡፡ አብሮነት፣ መረዳዳት፣ ሰው አክባሪነት፣ ለሌሎች መኖር፣ መከባበር፣ አርቆ አሳቢነት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ገፍታችሁ አትምጡብኝ ካልኾነ በስተቀር ሌሎችን አለመተንኮስ የአማራ ሕዝብ እሴቶች ናቸው፡፡
የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያውያን እህትና ወንድሞቹ ጋር በመኾንም በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ጉልህ ሚና አለው፡፡
ይሁን እንጂ የፖለቲካ ርዕዮቱን ለማሳካት የጠንካራ ሥነልቦና ባለቤት የሆነውን የአማራ ሕዝብ ማዳከም የትህነግ ዋነኛ የትግል ስልት ነበር፡፡ ይህ ጸረ አማራ ስብስብ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት የባላይነትን ለማስጠበቅ የሐሰት ትርክት ሰንዶ አማራ በሌላው ማኅበረሰብ እንዲጠላ አድርጓል፡፡ ይህ ድርጊቱም የአጭር ጊዜ ሳይኾን ለረጅም ዓመታት ታቅዶ የተሠራበት መኾኑን ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ተናግረዋል፡፡
ደርግን ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል የትግራይ አካባቢዎች ነጻ ከወጡ በኋላ ገና ጦርነቱ ሳይቋጭ አማራ ክልል የሚገኙ ተቋማት ተዘርፈው ወደ ትግራይ ተጭነዋል፡፡ ትህነግ መራሹ ግንባር የሀገሪቱን ስልጣን ከተቆናጠጠ በኋላም የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን በራሱ ቅርጽና ቁመና አደራጅቶ ሀገራዊ ስሜት ያላቸውን ግለሰቦች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና ተቋማትን የማፍረስና የማዳከም ሥራ ሠርቷል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ በዕውቀቱ ድረስ (ዶክተር) እንዳሉት የፋሺስት ኢጣሊያ የከፋፍለህ ግዛ አስተሳሰብ መዋቅራዊ ሥርዓት ተዘርግቶለት እንደ አንድ የጭቆናና የብዝበዛ መሳሪያ ኾኗል፡፡
አማራ በማንነቱ ምክንያት በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸም የማይገባው ድርጊት በአሸባሪው ትህነግ ተፈጽሞበታል፡፡ አሸባሪው ትህነግ አቅሙ የቻለውን በደል ሁሉ አድርሷል፤ ተገቢ የፖለቲካ ውክልና ጥያቄ እንዳይነሳ ሲያሸማቅቅ ቆይቷል፤ የኢኮኖሚ አሻጥር ሰርቷል፤ ሕዝብ ለሚያነሳቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጥያቄዎች ምላሹ እስራት፣ ግድያ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ መፈናቀል ነበር፡፡
የአማራን ሕዝብ ሥነልቦና በመጉዳት አንገቱን ለማስደፋት አሉ ያላቸውን አማራጮች ሁሉ ተጠቅሟል፤ ይሁን እንጂ ለቡድኑ ነገሮች በፈለገው እና በጥረቱ ልክ አልኾኑለትም፡፡ አሸባሪው ትህነግ ሞክሮት ያልቻለውም የአማራን የሥነልቦና ጥንካሬ ማዳከም ነው፡፡
በሕግ ማስከበር ዘመቻው ሽንፈትን ሲከናነብ በማይካድራ የፈጸመው ጭፍጨፋም ቡድኑ እየሞተ እንኳን ለሕዝቡ ያለውን ጥላቻ የሚያሳይ ነው፡፡
ከሰሞኑ የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም መደረጉና መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ለቅቆ እንዲወጣ ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ የአሸባሪው ቡድን አባላት የውዥምብር ወሬ ማሰራጨታቸውን ተያይዘውታል፡፡
በአማራ ሕዝብ ላይ ጥቃት እንደሚፈጸምም ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ይፋ አድርጓል፡፡
እንደ ዶክተር በዕውቀቱ ማብራሪያ የኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ደካማ ሀገር መኾን ለብዙ ነገር ተጋላጭ ያደርጋታል፡፡ ስለ አሸባሪው ትህነግ ሲታሰብ ደግሞ በርካታ ኀይሎች ከጀርባው እንዳሉ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ከዓባይ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ብዙ ፍላጎት ያላቸው ተዋንያን አሉ፡፡ ይህም ለሀገሪቱ ሳንካ እንደሚኾን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ምንም እንኳን ትህነግ ምንም ነገር የማድረግ አቅሙ የተንኮታኮተ ቢኾንም የአማራ ክልልም ኾነ የፌዴራል መንግሥት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የእነዚህን ኀይሎች አካሄድ ባገናዘበ መልኩ መኾን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ጥሩ አመራር ከተሰጠው የማይሻገረው ችግር እንደሌለ አሳይቷል፤ አሁንም የክልሉ ሕዝብ ከመሪዎቹ ጎን በመሰለፍ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን በብቃት መመከት እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ