
የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያደርገውን ስብሰባ የሚቃወም ሰልፍ ማምሻውን በኒው ዮርክ ይካሄዳል።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ)
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት የሚያካሄደውን ስብሰባ በመቃወም ዛሬ ማምሻውን በሚካሄደው ሰልፍ ለድርጅቱ የሚሰጥ ደብዳቤ መዘጋጀቱም ተገልጿል።
የጸጥታው ምክር ቤት ግብጽና ሱዳን ባቀረቡት ጥያቄ አማካኝነት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ዛሬ እኩለ ሌሊት ላይ ስብሰባ ያደርጋል።
በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምክር ቤቱ የጠራውን ስብስባ በመቃወም ኒው ዮርክ በሚገኘው የተመድ መሥሪያ ቤት ተገኝተው ሰልፍ እንደሚያደርጉ በዋሺንግተን ዲሲ ሰላምና አንድነት ግብረኃይል ኢትዮጵያ አባል አቶ ዳዊት አላምቦ ገልጸዋል።
ሰልፉ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ከ30 ድረስ እንደሚካሄድና በሺዎች የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርሲ፣ ቦስተን፣ ኮኔቲከት፣ ቨርጂኒያ፣ ዴልዌር፣ ፔንሲልቫኒያ፣ አትላንታ፣ ዋሺንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና በሌሎች አካበቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሏል።
“የጸጥታው ምክር ቤት በሕዳሴ ግድቡ ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ግብነት ማቆም አለበት” የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ ዋንኛው የሰልፉ ዓላማ እንደሆነ ነው አቶ ዳዊት የጠቆሙት።
የሰልፉ ተወካዮች ለጸጥታው ምክር ቤት የተጠራውን ሰልፍ በመቃወም የተዘጋጀውን ደብዳቤ ለድርጅቱ ያስገባሉ ብለዋል።
የደብዳቤው ይዘት ኢትዮጵያ ሕዝቧን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆንና ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በትብብር ማደግ እንጂ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት የሚያስረዳ እንደሆነ አመልክተዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ተመድ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት በደብዳቤው ላይ መስፈሩንም ነው አቶ ዳዊት ያስረዱት።
“ኢትዮጵያ የውኃ ሃብቷን የመጠቀም መብቷን ማንም ሊከለክላት አይችልም፣ ኢትዮጵያ በጋራ የመጠቀም ፍላጎት እንጂ ማንንም የመጎዳት ፍላጎት የላትም፣ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን አፍራሽ ተጽእኖ ማቆም አለበት እንዲሁም ተመድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለበትም” የሚሉ ሐሳቦችን ያዘሉ መልዕክቶች በሰልፉ እንደሚተላለፉ ጠቁመዋል።
የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች በአሜሪካ የሚኖሩ ግብጻውያን በኒው ዮርክ ከተማ ሰልፍ እንደሚያደርጉ መረጃ እንዳላቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተፈቀደላቸው ቦታ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት ብቻ እንደሚያስተላልፉና የግብጽ ሰልፈኞችም ባላቸው መብት ተጠቅመው ሐሳባቸውን ያስተላልፋሉ” ብለዋል።
ሰልፉ በዋሺንግተን ዲሲ ሰላምና አንድነት ግብረኃይል ኢትዮጵያና በኒው ዮርክ የሚገኙ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሰልፉን በጋራ ማዘጋጀታቸውን አመልክተው ኢትዮጵያዊያን ኹሉ በሀገራቸው ጉዳይ አንድ በመሆን የውጭ ጫናዎችን እንዲመክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4