
የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ግብር ከፋዮች ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የገቢ ዕቅዱ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ግብርን በተቀላጠፈ
መልኩ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ “ገቢያችን ለሕልውናችን” በሚል መርህ ከዛሬ ጀምሮ በ10 ቀናት ውስጥ ከደረጃ ሐ
ግብር ከፋዮች ሙሉ በሙሉ ግብር ለመሰብሰብ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ እቅዱ ግብር ከፋዮች የአገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆኑ፣
ለቅጣት እንዳይጋለጡና በንቅናቄ ግብር የመክፈል ባሕል እንዲዳብር ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ቢሮው ትኩረቱን ወደ ሌሎች ሥራዎች
እንዲያዞርም ግብር የመሰብሰብ ተግባሩ በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ አለበት ተብሏል፡፡
ክልሉ ካለበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ሀብት መሰብሰብ አስፈላጊ ነው፤ ይህም ወደ ንግድ መረቡ ያልገቡትን ሕጋዊ ለማድረግ
ያግዛል ነው የተባለው፡፡ ለዚህም 206 ቋሚ የግብር መሰብሰቢያ ጣቢያዎች አሉ፤ ሂደቱን ቀልጣፋ ለማድረግም 700 ገደማ
ተጨማሪ ጊዜያዊ ጣቢያ ተዘጋጅቷል፡፡ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓትም መዘርጋቱን የአማራ ክልል
ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ኀላፊ ብዙዓየሁ ቢያዝን እንዳሉት ባንኮች የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች በአሃዝ ደረጃ ከክልሉ አጠቃላይ ግብር ከፋዮች 90 በመቶ ገደማ ይሆናሉ፡፡ በነባር ግብር ከፋዮች
ስሌት 641 ሚሊዮን 606 ሺህ 100 ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን አዳዲስ ግብር ከፋዮች ሲካተቱ ሊጨምር እንደሚችል
ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡
የግብር ከፋዮች ግብር በወቅቱ የመክፈል ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡ በዛሬ ውሎ ጥሩ አፈጻጸም የታዬባቸው
አካባቢዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
ግብር ከፋዮች የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በውል ተገንዝበው ግዴታቸውን በወቅቱ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የገቢ ሰብሳቢ ተቋሙ ሠራተኞችም ከሌሎች ጊዜያት በተለዬ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ በአንድ ቀን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ግብር ሰብስቦ ውሏል፡፡ በአስተዳደሩ በ10 ቀናት
ውስጥ ከ20 ሺህ 452 ግብር ከፋዮች ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያሉ የሥራ ኀላፊዎችና ባለሙያዎች ልዩ
ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው ተብሏል፡፡ በዛሬው ውሎ ጥሩ እንቅስቃሴ እንደነበር የአስተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ
ውባንተ ዳምጤ ተናግረዋል፡፡ የታቀደውን ለማሳካትም በቀጣይ ቀናት ተገቢው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ከ306 ሺህ በላይ ነባርና 55 ሺህ ገደማ አዳዲስ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች እንዳሉም ቢሮው አስታውቋል፡፡ ከ109
ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤትና የድርጅት ኪራይ ግብር ከፋዮች እንደሚኖሩም ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በትዊተር https://bit.ly/37m6a4m