
በዘንድሮው ክረምት በዓባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የጥምር ደን ችግኝ የሚተከል መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ በአግባቡ በማከናወን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል በመከላከል የአገልግሎት ጊዜውን ለማራዘም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ወሳኝ ነው፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲ እንደገለጹት፤ ለዘንድሮ የአረንጓዴ ልማት መርኃ ግብር ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቶ እየተተከለ ነው።
በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ ብቻ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ እንደሚተከልም ገልጸዋል።
በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎችን በማጠናከር የህዳሴ ግድቡን ከደለል ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ተፋሰሱ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ በርካታ ወረዳዎችን እንደሚሸፍን የገለጹት አቶ ሳኒ፤ “በእነዚህ አብዛኛው አካባቢዎች የችግኝ ተከላ ተጀምሯል” ብለዋል።
የግድቡን ውኃ የመያዝ አቅም የሚጎዱ ሁኔታዎችን መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የግድቡን ህልውና መጠበቅ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ዓባይን አልምቶ ለመጠቀም በዲፕሎማሲው መስክ እየተደረገ ያለው ትግል የግድቡን ህልውና በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድም መደገም እንዳለበት ገልጸዋል።
የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በበኩላቸው የህዳሴ ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአህጉሩና ለዓለም ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
በተለይ የውኃ ሃብትን ለማሳደግ፣ ለኃይል ማመንጫ፣ ለብዝኃ ህይወት ጥበቃና ለደን ልማት እንዲሁም ለሥራ እድል ፈጠራ ጠቃሚ መሆኑን አመላክተዋል። በመሆኑም የአረንጓዴ ልማቱ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉና ለአካባቢ ጥበቃ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በትዊተር https://bit.ly/37m6a4m