
ለምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ዋንጫ ውድድር በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከሐምሌ 10/2013 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ ለሚካሄደው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ዋንጫ ውድድር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው አዘጋጅ ኮሚቴ ገለጸ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሥራ አስፈፃሚ አባልና የአዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አበበ ገላጋይ ወድድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ከአማራ ክልል መንግሥትና ከስፖርት ኮሚሽን ጋር የቅንጅት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። ዝግጅቱን የተሳካ ለማድረግ የመስተንግዶ፣ የጸጥታ እና ሌሎች ንዑስ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል ተብሏል።
ወድድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አዲስ አበባ እና ባሕር ዳር ላይ የተቋቋሙት ሀገር አቀፍ ኮሚቴዎችም በቅንጅት እየሠሩ መኾኑ ተጠቁሟል።
ውድድሩ ያለምንም የፋይናንስ ችግር እዲካሄድ ኮሚቴው ስፖንሰሮችን በማፈላለግ የገንዘብ አቅሙን አጠናክሯል ነው የተባለው።
ውድድሩ ከሚካሄድበት የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተጨማሪ የልምምድ ቦታ ችግር እንዳይኖር አማራጮች ተቀምጠዋል። በዚህ ረገድ ምንም አይነት ክፍተት እንደማይኖር አረጋግጠናል ነው ያለው የፌዴሬሽኑ መግለጫ፡፡
ውድድሩ የኮሮናቫይረስ መከላከል ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ እንደሚካሄድና የተወሰኑ ደጋፊዎች ስታዲየም እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡ የስታዲየሙ የመያዝ አቅም 100 ሺህ ደጋፊ ይይዛል፤ እስከ 25 ሺህ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም መግባት ይችላሉ ነው የተባለው።
ከሐምሌ 10/2013 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው የሴካፋ ውድድር 11 የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን -ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ