
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የአማራን ሕዝብ ህልውና ለማስጠበቅ ከሚሠሩ የፖለቲካ ኀይሎች ጋር ሁሉ በጋራ ለመሥራት መዘጋጀቱን አዴኃን ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ዴሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫው በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና በአማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ በሚመለከት የድርጅቱን አቋም የሚገልጽ ነው፡፡
“የአማራ ሕዝብ የዘመናት ችግሮች ባዕዳን ናቸው” የሚለው የድርጅቱ መግለጫ ሂሳብ ለማወራረድ የተዘጋጁትን የውስጥ ቡድኖች ደግሞ ባዕዳን ያሰማሯቸው “የረጅም ዘመናት ባንዳዎች” ናቸው ሲል ይገልጻቸዋል፡፡ ንቅናቄው ከሁለቱም ቡድኖች የሚሰነዘረውን የሉዓላዊነት ጥሰት እና የሕልውና አደጋ አጥብቆ እንደሚቃዎም እና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል፡፡
የአዴኃን የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪ አቶ ምርጫው ስንሻው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ጫና፣ የአሸባሪው ትህነግ ጠብ አጫሪ ትንኮሳ እና የአማራ ሕዝብ ነባር ርስቶችን ፍለጋ ተከትሎ ከውስጥም ከውጭም የሚፈጠር ጫና ተገቢነት የለውም ነው ያሉት፡፡
አሸባሪው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ ሲያደርሰው የነበረው ጥላቻ እና ዘር ማጽዳት የሚረሳ አይደለም ያለው የንቅናቄው መግለጫ ያንን የግፍ ዘመን ለመድገም ለሚዳዱ ቡድኖች ቆመን የምናይበት ዘመን አክትሟል ብሏል፡፡
የአማራ ሕዝብም ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን አስጠብቆ በጋራ ሊቆም እንደሚገባ አዴኃን በመግለጫው ጠይቋል፡፡
የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ድርጅቶች ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ ጠንቅቀው ያውቃሉ ያሉት አቶ ምርጫው ንቅናቄው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የአማራን ሕዝብ ህልውና ለማስጠበቅ ከሚሠሩ የፖለቲካ ኀይሎች ጋር ሁሉ በጋራ ለመሥራት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
የተዳከመች ኢትዮጵያን ማየት የዘወትር ህልማቸው የሆነው የውጭ ኀይሎች የሰሜን ኢትዮጵያን ወቅታዊ ግጭት እና የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት አስታከው በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጡትን ጣልቃ ገብነት አዴኃን አጥብቆ ይቃዎማል ብለዋል፡፡ ለዚህም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና የአዴኃን ደጋፊዎች የውጭ ኀይሎች የሚያደርጉትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት አጥብቀው እንዲቃዎሙ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ