ከቅድመ ነገራ ጳጉሜን 4 እስከ ጥቅምት 24 የአሸባሪው ትህነግ ሴራ፡፡

198
ከቅድመ ነገራ ጳጉሜን 4 እስከ ጥቅምት 24 የአሸባሪው ትህነግ ሴራ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት በሕግ ማስከበር ዘመቻ ውስጥ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ያሳለፍነው የግፍ ዘመን ይብቃ ብለው ትህነግ መራሹን ቡድን ከቤተ መንግሥት አስወጡት፡፡ ከቤተ መንግሥት ከተባረረ በኋላም ቡድኑ ልዩነቶችን በይቅርታ ለማለፍ ሕዝብ እድል ቢሰጠውም መቀበል ግን አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል ወታደራዊ ክህደት እና ጥቃት ፈጸመ፡፡ የተፈራው አይቀሬ ሆነ ጦርነቱን ትህነጋዊያን ጀመሩት ኢትዮጵያዊያንም በላቀ ጀብዱ ዳር አደረሱት፡፡ የዚህን ሕግ የማስከበር እርምጃ ከውልደቱ እስከ ልደቱ፤ ከሂደቱ እስከ ሽኝቱ በተከታታይ ክፍል እንቃኛለን፡፡
ከ12ኛው የሐዋሳው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ማግስት ጀምሮ የተካረረው የለውጥ ኀይሉ እና የአሸባሪው የትህነግ ነባር አባላት ቅራኔ ውልድ ነው፡፡ በእርግጥ በሐዋሳው ድርጅታዊ ጉባኤ የለውጥ ሂደቱን የተቀበለ የኢትዮ-ኤርትራን እርቀ ሰላም ያከበረ መስሎ በአድናቆት ጭምር ቢወጣም መቀሌ ሲገባ ግን ነገሮች በተገላቢጦሽ ይዘመሩ ጀመር፡፡
በታየው የለውጥ ሂደት ደስተኛ ያልነበረው ትህነግ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ራሱን አግልሎ መቀሌ ሲከትም ልዩነቶቹን በግልጽ ማንፀባረቅ ጀመረ፡፡ የግንባሩ አባል ድርጅቶች እና ደጋፊዎች ውህደት የኮመዘዘው፣ የኢትዮ-ኤርትራ እርቀ ሰላም መፋጠን የሰቀዘው፣ የህሊና እስረኞች መለቀቅና አሸባሪ የተባሉ ድርጅቶች ወደ ሀገር መመለስ ያንገሸገሸው እና የምጣኔ ሃብታዊ እይታዎች መቀየር ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባው አሸባሪው ትህነግ ጉዳዩን ‹‹የትግራይ ሕዝብን በኀይል ማንበርከክ›› ነው ሲል የዳቦ ስም ሰጠው፡፡
የቃላት ጦርነት በየአውዱ ጎልቶ የተስተዋለበት እና ቀዝቃዛ ሽኩቻን ያስተናገደው ያለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞ አዲሱ የለውጥ ኀይሉና የትህነግ ቡድን በግልፅ ተለይተው ታዩበት፡፡ ኢትዮጵያዊነትን አቀንቃኞቹ አዲሱ የለውጥ ኀይሎች እና መቀሌ የመሸገው ጉምቱ የህወሐት የቀድሞ አድራጊ ፈጣሪዎች በሁለት ጎራ ግንባር ቀደም ተዋንያን ኾነው ብቅ አሉ፡፡
የአማራ ምድርን እና የአማራ ሕዝብን የፖለቲካ ትኩሳቱ የስበት ማዕከል ያደረገው ፍጥጫ በሀገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ከከሚሴ እስከ ደሴ፣ ከጎንደር እስከ ሞጣ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ባህር ዳር፣ ከኦሮሚያ እስከ ሶማሌ፣ ከቤንሻንጉል እስከ ደቡብ የተቀበሩትን የጥፋት ፈንጆች ክር ለ113 ጊዜ እየወጠረ አፈነዳቸው፡፡ የሚፈነዱት የጥፋት ፈንጂዎች ዒላማ በዋናነት በኢትዮጵያዊነት ስሜት ተጠምቀው በቆረቡት የአማራ ሕዝቦች ላይ ያነጣጠሩ ቢኾኑም ፍንጣሪው ግን ሌሎቹንም ማግኘቱ አልቀረም ነበርና ተጠቂው አማራ ተጎጂዋ ደግሞ ኢትዮጵያ አደረጋት፡፡
ለ113 ጊዜ ታስቦባቸው እና ታቅዶባቸው ከፈነዱት የግጭት ፈንጂዎች በስተጀርባ በፈፃሚነት እና በአስፈፃሚነት ወይም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ትህነግ ተዋናኙ ነበር፡፡ አልፎ አልፎም በነቀፋም ይሁን በማስተባበያ ትህነግ ለውንጀላዎቹ መልስ የሰጠባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ እነዚህ የግጭት ፈንጂዎች እና መልሶቻቸው በኢትዮጵያ ያለውን የኀይል አሰላለፍ በግልፅ አሳየ፡፡
የኀይል አሰላለፉም ኢትዮጵያን በመበታተን እና አንድ በማድረግ በኩል ጎልቶ ወጣ፡፡ ኢትዮጵያን አንድ ማድረግም ኢትዮጵያዊያንን አንድ አይነት እንደማድረግ ተቆጥሮ ‹‹አሃዳዊያን›› የሚል ውንጀላ በአሸባሪው ቡድን በኩል ደጋግሞ ተስተጋባ፡፡ እንደ ተሰጣ ጥሬ በሀገሪቱ ሁሉም አቅጣጫ የሚፈሰው የንፁሃን ደምም እንደራሴዎቻቸውን ሳይቀር በፓርላማ ውስጥ በእምባ እስከማራጨት ደረሰ፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ቤተ አምልኮዎች፣ አደባባዮች እና ሕዝባዊ ጎዳናዎች፣ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች እና ታላላቅ ህንፃዎች ሳይቀሩ ለንፁሃን ደም መፍሰስ የተለዩ የጥቃት ቦታዎች ተደርገው ተወሰዱ፡፡ በየወቅቱ እና በየአቅጣጫው በሚፈጠሩ የጥፋት ድግሶች ለቅሶ፣ ዋይታ፣ ትችት፣ ውንጀላ እና መግለጫ ተደጋግሞ በሁለቱም ጎራ ሲደመጥ ሕዝብ ግራ ተጋባ፡፡
ገድሎ ቀድሞ የሚያለቅሰው ቡድኑ የብዙኀኑን ለቅሶ ሳይቀር ቀድመው ይቀሙት ጀመር፡፡ ይህን ሁሉ ውጥንቅጥ በሰከነ ሁኔታ ያስተዋለው ሕዝብ ቀጣይ ደም አፋሳሽ ጦርነት ስለመኖሩ አልተጠራጠረም ነበር፤ ብዥታው የአጀማመሩ ሂደት እንጅ፡፡ የአሸባሪዎቹ ቡድኖች የሃሳብ ልዩነት የማይታረቅ ኾኖ እያለ ለልዩነቱ ሽብልቅ ለግጭቱ ነዳጅ የሚያቀርቡ ግልገል ኀይሎችም ግንባር ቀደም ተዋንያን ነበሩ፡፡ መቀሌ ሄዶ መሰብሰብ አጀንዳ ይዞ መመለስ ግልፅ የወጣ የአፍራሽነት ሥራቸው ኾነ፡፡
‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ መቃረብ እና የግልገሎቹ የተጣረሰ ፍላጎት ምርጫው ለልዩነቱ ሰርግና ምላሽ ኾነ፡፡ ከምርጫው በፊት ሀገራዊ እርቀ ሰላም እና የጋራ መግባባት መቅደም ይኖርበታል የሚሉት እና ምርጫውን ማካሄድ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው የሚሉት ኀይሎች ከዚያም ከዚህም በዙ፡፡
ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታህሳስ ላይ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ለምርጫ ውዝግቡ የከፋ አጋጣሚ ሆኖ ተከሰተ፡፡ ከኢትዮጵያ ቀድመው የምርጫ ድግሳቸውን ያራዘሙ ከ50 በላይ የዓለም ሀገራት ቢኖሩም ኢትዮጵያ ግን ስለጉዳዩ እልባት ላይ ለመድረስ ሕገ መንግሥታዊ መላ ፈለገች፡፡ በኮሮናቫይረስ የስርጭት ወቅት ምርጫ ማካሄድ በመራጩ ሕዝብ ህይዎት ላይ መፍረድ ቢኾንም ምርጫውን ማራዘም ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት እና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን መናድ ነው የሚሉ ቡድኖች ተፈጠሩ፡፡
ትህነግ ምርጫውን አለማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት እና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን መናድ ነው የሚል አቋም ይዞ ብቅ አለ፡፡ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በወቅቱ ቀዳሚ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ አጀንዳ ኾኖ ቀልብ አንጠልጣይ ክርክሮችን፣ ውይይቶችን እና ሰጣገባዎችን አሰተናገደ፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ ከነአማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦቹ ለሕዝብ እንደራሴዎች ለውሳኔ ቀረበ፡፡ በእንደራሴዎቹ፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት እና በሚመለከታቸው አካላት ታይቶ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ›› እንዲሰጠው ተመራ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ አስተናግዶ እና የሀገሪቱ የመጨረሻ የስልጣን ባለቤቶች ውሳኔ አርፎበት ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘምም ተደረገ፡፡
ይህ ውሳኔ ግን ለትህነጋዊያን የማይዋጥላቸው ብቻ ሳይኾን ያሰቡትን ከማድረግ የማይመለሱ መኾናቸውን በግልጽ አሳየ፡፡ ቆመንለታል ከሚሉት ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት በተፃራሪ ክልላዊ የምርጫ ቦርድ አቋቁመው ለምርጫ ድግስ ቀነ ቀጠሮ ጳጉሜን 4/2012 ዓ.ም ቆረጡ፡፡ አያደርጉትም የሚሉት ቢበረክቱም በአዲስ ዓመት ዋዜማ ትግራይ ክልል ውስጥ ምርጫ አካሂደው ትህነግ እውቅና ያለው መንግሥት መመስረቷን ገለጸች፡፡
የአሸባሪው ትህነግ አመራሮችም ከምርጫቸው ማግስት ጀምረው ትግራይ ክልል መሆኗ ቀርቶ ሀገር ለመኾን እየዳዳት እንደኾነ በገደምዳሜው ነገሩን፡፡ በእርግጥ በቀጣይ የሁነቶችን ሂደታዊ ዑደት ጠብቀን የምናነሳቸው ሌሎች ዲፋክቶ ስቴታዊ ድርጊቶች ቢኖሩም የምርጫው ጉዳይ ግን በግልፅ የታየ አፈንጋጭነት ነበር፡፡ ከትግራይ ክልል ምርጫ በፊት እና ከምርጫው በኋላ መንግሥት ሕግን ለማስከበር የኀይል አማራጭ ወይም ሕገ መንግሥታዊ የእርምት እርምጃ ይወስዳል ተብሎ ቢጠበቅም ጉዳዩን በትግስት አለፈው፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት በትግራይ የተካሄደውን ምርጫ ‹‹ኢ-ሕገ መንግሥታዊ›› እንደሆነ በውሳኔ ገለጸ፡፡ ትህነጋዊያን በአንፃሩ ከመስከረም 25/2013 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ ሕጋዊ መንግሥት የለም ማለት ጀመሩ፡፡ በዚህ ሃሳባቸው ደግሞ ትንሽም ቢኾን ድጋፍ የሚሰጡ ኀይሎች ብቅ ብቅ ማለታቸው አልቀረም ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሲያዩት ቀላል የመሰለ ነገር ግን ከሕግ እና አስተዳደራዊ ስርዓት አንፃር ሲታይ የማያፈናፍኑ ውሳኔዎችን ቀስ በቀስ በሂደት ማሳለፉን ቀጠለ፡፡ ለተመረጡ አካላት እውቅና ነፈገ፣ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ያለውን ግንኙነት ከታችኛው የአመራር አካላት ጋር አደረገ፣ በጀት የሚለቀቀው ለክልሉ ሳይኾን ለተቋማት ኾነ እንዲሁም የብር ኖት ለውጥ፣ የቋሚ ሃብት ዝውውር እና ሽያጭ መልክ መያዝ ትህነጋዊያንን ተስፋ አስቆረጣቸው፡፡
እንደሌሎቹ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በገንዘብ ኖት ለውጥ ላይ የሰላ ትችት ያወርዳሉ ተብለው የተጠበቁት የትህነግ አንጃዎች ስብስብ የሆዳቸውን በሆዳቸው አድርገው የበዛ ትችት ከመሰንዘር ተቆጠቡ፡፡ በነገሮች በሳል እና ፈጣን ፖለቲካዊ እርምጃዎች የተወጠሩት ትህነጎቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ከቻሉ በድጋሜ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ለመመለስ ካልቻሉ ደግሞ በተደጋጋሚ የሚናገሩትን ሀገር የመበታተን ሴራ ጥንስስ ገቢር ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡
ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ማጋጨት፣ አማራን ማዕከል ያደረገ የዘር ማጽዳት ዘመቻ፣ ታዋቂ ግለሰቦችን እና ፖለቲከኞችን ማዕከል ያደረገ ግድያ፣ ዲጂታላይዝድ የሃሰት መረጃ ስርጭት፣ ዲፕሎማሲያዊ እና የውጭ ግንኙነት ህጸጽ፣ የኢትዮ-ኤርትራ እርቀ ሰላምን ማጣጣል፣ ግለሰባዊ ስድብ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ያልተሞከረ ሴራ ያልተጎነጎነ ሸር አልነበረም፡፡
እነዚህ ሁሉ ግን በመሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው ላይ ለውጥ ጠብ ማድረግ ስላልቻሉ ለሌላ ተልዕኮ እና ሽብር መዘጋጀታቸው ግልጽ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ቀይ መስመሩን አልፈው የማይደፈረውን ደፈሩ፤ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት በአማራ ሕዝብ ላይ ጥቃት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ ፈፀሙ፤ ይህም ወደ ግልፅ ጦርነት አመራ፡፡ ቀጣይ ጉዳዮችን በክፍል ሁለት እንመለስበታለን፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የደገፈው ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅት የመብሰያን ጊዜን ከ6 ሰዓት ወደ አንድ ሰዓት የሚያወርድ ማብሰያ እያመረተ ነው።
Next articleየኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የአማራን ሕዝብ ህልውና ለማስጠበቅ ከሚሠሩ የፖለቲካ ኀይሎች ጋር ሁሉ በጋራ ለመሥራት መዘጋጀቱን አዴኃን ገለጸ፡፡