
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የደገፈው ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅት የመብሰያን ጊዜን ከ6 ሰዓት ወደ አንድ ሰዓት የሚያወርድ ማብሰያ እያመረተ ነው።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሃመድ (ዶ.ር)፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሚ እና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህወይት ወልደሃና (ዶ.ር) በቦሌ ለሚ ኢንደስትሪ ፓርክ እየሠራ የሚገኘው ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅት የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
ድርጅቱ ከቡና አተላና ገለባ፣ ከጫት ገረባ፣ ሳጋቱራና ከመሳሰሉት የቆሻሻ ውጋጆች ኃይል በመጠቀም መሥራት የሚያስችል እና ይህንን የሚጠቀም ስቶቭ እያመረተ ይገኛል።
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ማብሰያዎች ከአካባቢ ጋር የሚስማሙና ፍጆታን የሚቀንሱ ናቸው።
ከቆሻሻ ውጋጅ የሚገኘውን ኃይል እና ማብሰያውን የሚያመርተው ድርጅቱ በቀን እስከ 200 የሚደርስ “ቋይቶን” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ስቶቭ የማምረት አቅም ላይ ደርሻለሁ ብሏል።
የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ፀጋየ ነጋ የቋያቶንን ንድፍ ፣እቃውን መፈብረክና ለቋይቶን የሚሆን ተቀጣጣይ በአንድ ላይ በማምረት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ውስጥ ብቸኛ ነን ብለዋል።
ተቀጣጣዩ ለማብሰያነት ካገለገለ በኋላ ወደ ከሰልነት ይቀየራል፤ ድርጅቱ ይህንን ከሰል ከደንበኛው ድጋሚ በመግዛት ሥራ ላይ ያውለዋል።
በብዛት ለምግብነት የሚሠራን ወጥ ምሳሌ ያደረጉት ፕሮፌሰሩ 100 ሊትር ወጥን ለማብሰል 6 ሰዓት ይፈጅ የነበረውን የማብሰያ ጊዜ ወደ 1 ሰዓት የሚያወርድ ማብሰያም መሥራታቸውን ጠቁመዋል።
በቦሌ ለሚ ኢንደስትሪ ፓርክ እየሠራ የሚገኘው ይህ ድርጅት በፓርኩ ውስጥ የተሰጠውን የመስሪያ ቦታ ልቀቅ በመባሉ ምክንያት ስጋት እንዳደረበት ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ተቋማቸው ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን የሚያደግፍበት “የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች አዋጅ” አዘጋጅቶ መፀደቁን እየተጠባበቀ መሆኑንና ያሉ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሚ በበኩላቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ድርጅቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የመሥሪያ ቬድ ኪራይን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግለት ቆይቷል።
ከሰሃራ በታች 600 ሚሊየን አካባቢ የስቶቭ ፍላጎት አለ፤ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ጥቂቶች ብቻ ናቸው ተብሏል። መረጃው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ