
”ደጀን ወደ ሆነው ሕዝባችን ስንገባ የተደረገልን አቀባበል ሠራዊቱን ያስደመመ ነው” ኮሎኔል ሻምበል በየነ የ23ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ
ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ደጀን ወደ ሆነው ሕዝባችን ስንገባ የተደረገልን ደማቅ አቀባበል ሠራዊቱን ያስደመመ እንደነበር የ23ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሻምበል በየነ አስታወቁ። ጁንታው ገደልን ማረክን እያለ ማሳሳት የኖረበት ባህሪው መሆኑን አመልክተዋል።
ኮሎኔል ሻምበል በየነ (ባለከዘራው) እንደገለጹት በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ ስንደርስ በሕዝቡ የተደረገልን አቀባበል ደማቅ እና ሠራዊቱ የሕዝብ ሠራዊት መሆኑን በተጨባጭ ያሳየ ነው።
እኔ በግሌ የህዝቡን አቀባበል የምጠብቀው ቢሆንም፤ በሠራዊቱ ዘንድ በዚህ ደረጃ አቀባበል ይደረጋል ብሎ አልጠበቀም ነበር። በያለፍንባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ ለሠራዊቱ ያለውን ፍቅር የገለጸበት መንገድ ከፍ ያለ የሞራል ስንቅ የሚሆን ነው ብለዋል።
ሕዝቡ ለሠራዊቱ የሚበላም የሚጠጣም በማቅረብ ለሠራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተግባር አሳይቷል። በተለያየ ደረጃ የሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል አቀባበሉ የተለየ ነው፤ ይህ በጣም ተአምር ነው። በእዚህ ምክንያት መከላከያ ያቀረበልንን ምግብ መጠቀም አልቻልንም ሲሉ አመልክተዋል።
ጁንታው የውሸት ፕሮፖጋንዳን እንደ አንድ የውጊያ ስልት በማድረግ ይጠቀማል፤ በዚህም ያልማረከውን ማረኩ፤ ያልገደለውን ገደልኩ ማለቱ አዲስ አይደለም። ‹‹ባለከዘራው ኮሎኔልን ከበነዋል፣ ማርከነዋል፣ ገድለነዋል›› የዚሁ ባህሪው መገለጫ ነው።
እኔን ማረኩ ገደልኩ ሲል የነበረው እኔ ከሌላው አመራር የተለየሁ ሆኜ ሳይሆን በሕዝቡና በሠራዊቱ ያለኝን ተቀባይነት ግምት ውስጥ በማስገባት ላሰለፋቸው ታጣቂዎች የተዳከመ የሞራል አቅም ለመገንባት እንደሆነ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ