
“የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እየተከናወነ ያለው ሦስቱ ሀገሮች በፈረሙት የመርህ ስምምነት መሰረት ነው”
ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እየተከናወነ ያለው
ሦስቱ ሀገሮች በፈረሙት የመርህ ስምምነት መሰረት መሆኑን የግድቡ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌዲዮን
አስፋው ገለጹ።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን እኤአ በ2015 በመሪዎቻቸው አማካኝነት በሱዳን ካርቱም የህዳሴ ግድቡን ድርድር አስመልክቶ
የመርሆች ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።
የመርህ ስምምነቱ አስር አንቀጾችን ያካተተ ሲሆን የሦስቱንም ሀገሮች ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ለማረጋገጥ ያለመ
መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በተስማሙት የመርህ ስምምነት መሰረት ሁለተኛው ዙር የግድቡ የውኃ ሙሌት እየተከናወነ
መሆኑን የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው ለኢዜአ ገልጸዋል።
በህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌት ላይ የሦስቱም ሀገሮች ባለሙያዎች የተስማሙባቸው ነጥቦች የተቀመጡ መሆኑን አስታውሰው
ሀገሮቹ በዚሁ መሰረት መስማማታቸውን አስረድተዋል።
ግብጽና ሱዳን በመርሆች ስምምነት ውስጥ ሁለት ጥናቶች እንዲካሄዱ የሚያስቀምጥ ቢሆንም ግብጽና ሱዳን ጥናቱ
እንዳይካሄድ ሲያስተጓጉሉ ነበር ብለዋል።
ሀገሮቹ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በ15 ወር ውስጥ ሁለት ጥናቶችን ማከናወን እንዳለባቸው ቢያስቀምጥም ጥናቶቹ እንዳይካሄዱ
ግብጽና ሱዳን በያዙት ግትር አቋም ሳይሳካ ቀርቷል ነው ያሉት።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፤ ግብጽና ሱዳን የግድቡን ውኃ ሙሌት በተመለከተ የሚሰጡትን የተዛባ መረጃ ሊመረምር እንደሚገባም
መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመርሆ ስምምነቱ መሰረት የግድቡን ውኃ ሙሌት የተመለከቱ አንቀጾች በግብፅና ሱዳን የውኃ ባለሙያዎች የሚታወቁና
ስምምነት የተደረሰባቸው መሆኑንም አንስተዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m