
የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በ10 ቀናት ውስጥ ከፍለው እንዲያጠናቅቁ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን
የምዕራብ ጎጃም ዞን ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከሐምሌ 1/2013 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም የደረጃ “ሐ” ግብርን በንቅናቄ
ለመሠብሰብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የምዕራብ ጎጃም ዞን ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የዞኑ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አወቀ አይናለም የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1/2013 ዓ.ም ጀምሮ በ10
ቀናት ውስጥ በንቅናቄ ግብራቸውን እንዲከፍሉ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል::
ባለፈው ዓመት የደረጃ “ሐ” ግብርን አስከ ሐምሌ 14/2012 ዓ.ም እንዲሰበሰብ በማድረግ ዞኑ የተሻለ አፈጻጸም እንደነበረው
ያስታወሱት ኀላፊው ከባለፈው ዓመት ልምድ በመውሰድ እና ክልሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ግብርን በተቀመጠለት ጊዜ
ለመሰብሰብ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አቶ አወቀ ነግረውናል::
የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በተቀመጠው ጊዜ ግብራቸውን በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ የጠየቁት አቶ አወቀ
የሥራ ኀላፊዎች፣የሚመለከታቸው አጋርና ባለድርሻ አካላት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ግብር እንዲሰበሰብ አስፈላጊውን ትብብር
እንዲያደርጉም ጠይቀዋል::
በምዕራብ ጎጃም ዞን ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በግብር ዘመኑ ከ34ሺህ 721 ግብር ከፋዮች ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ
ለመሠብሠብ በዕቅድ መያዙን ለማወቅ ተችሏል::
ዘጋቢ፡-ዘመኑ ይርጋ -ከፍኖተ ሰላም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m