
የኢትዮ – ሩሲያ 11ኛው ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር የጋራ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሁለቱን ሀገሮች ወታደራዊ ትብብር ማጠናከርን ዓላማ ያደረገው ይህ ውይይት ፣
ከዚህ በፊት የተደረገውን 10ኛውን የወታደራዊ ቴክኒክ ፕሮግራም አጀንዳ አይቶ ያጸድቃል ነው የተባለው፡፡
በአሁኑ በ11ኛው ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር ላይም እየመከረ ይገኛል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ መኮንኖች ክበብ እየተካሄደ የሚገኘው ምክክር ፣ የኢትዮጵያን እና የሩሲያን ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ፣ ክህሎት እና
እውቀት ማሳደግ ላይ ነው ያተኮረው፡፡
የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ፣ ሁለቱ ሀገሮች ከ1898 ጀምሮ በዲፕሎማሲ ፣ በወታደራዊ ፣
በኢኮኖሚ ፣ በፖለቲካ እና በማኅበራዊ መስክ ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል ፡፡
በአሁኑ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ
መኮንን ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው ከመከሩ ወዲህ የሀገራቱ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ስታካሂድ ሩሲያ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንደሆነ አቋም ይዛ በመንቀሳቀሷ ፣ በስድስተኛው
ሀገራዊ ምርጫ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ ወዳጅነቷን በማሳየቷ ሚኒስትር
ደኤታዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሩሲያ ፌዴሬሽን የወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር ምክትል ዳይሬክተር ፑንቹክ አናቶሊ በኢትዮጵያና ሩስያ መካከል የቆየ ወዳጅነት
አለ፡፡ በወታደራዊ መስክ ብዙ የኢትዮጵያ መከላከያ አባላት በሩሲያ ስልጠና ወስደዋል፡፡
ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር የጋራ ውይይትም የሁለቱን ሀገሮች የቆየ ወዳጅነት የሚያሳድግ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡
የመከላከያ ኢንዱስትሪ እና ደጀን አቭዬሽንን የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ እየተደረገ ያለውን ሥራ በጋራ እንደሚያጎለብቱ
መግለጻቸውን ከመከላከያ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
