ማን ነው አምባሳደር?

158

ማን ነው አምባሳደር?
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ዲፕሎማሲ ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ የተሸከመ ቃል ቢሆንም በውጭ መንግሥታት ወይንም
ድርጅቶች መካከል ያለውን ልዩነት በውይይት፣ በድርድር ወይም ሌሎች ሰላማዊ መንገዶችን በመጠቀም ተጽዕኖ ማሳረፍ
የሚያስችል ጥበብ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ዲፕሎማሲ አንድ መንግሥት ከሌላው ዓለም ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ያስቀመጠውን ግብ እና ስትራቴጂ የሚወክል የውጭ
ፖሊሲ ዋነኛ መሣሪያ እንደኾነም ይተነትናሉ፡፡
የሀገሮች ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች፣ ውሎች፣ ትብብሮች እና ሌሎች የውጭ ፖሊሲ መገለጫዎችም በብዛት የዲፕሎማሲያዊ
ድርድሮች እና ሂደቶች ውጤት ናቸው፡፡ አሁን ላይ አብዛኛው የዲፕሎማሲ ሥራ በየሀገሮቹ መንግሥታት ዘንድ ዕውቅና ባላቸው
ልዑካን እና አምባሳደሮች ተወስኖ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች በኩል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ሥራን የበለጠ ለማጠናከር በመንግሥት እውቅና የተሰጣቸውን ተቋማት ከማጠናከር ባለፈ በተለያዩ
ክፍለ ዓለማት ተበታትኖ የሚኖረውን ዜጋ በማሰባሰብ በዲፕሎማሲያዊው ሥራ እንዲሳተፍ እና እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር
እንዲኾን መሥራት ሌላው አማራጭ ነው፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ሰኔ 28/2013 ዓ.ም በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ
ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ ለምክር ቤት አባላት እንዳሉት ዓለም ላይ ካለው ጂኦፖለቲክስ እና ሀገሪቱ አሁን ካለችበት
ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የሀገሪቱን ዲፒሎማሲያዊ ሁኔታ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሰረት አሁን ካሉት 60 የሚጠጉ ኤምባሲ
እና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑትን በመቀነስ አምባሳደሮች ሀገር ውስጥ ኾነው የዲፕሎማሲውን ሥራ
እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡
የዲፕሎማሲውን ሥራ ለማጠናከርም በርካታ ወጣቶች ሰልጥነው ወደ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መቀላቀላቸውን
አብራርተዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከአንድ አምባሳደር ባልተናነሰ መልኩ ያለምንም ክፍያ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የዲፕሎማሲ ሥራ
እየሠሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት፡፡ በቀጣይም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን
ለሀገራቸው አምባሳደር ኾነው እንዲሠሩ ይደረጋል ማለታቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሱት ሐሳብ አኳያ ግብጾች የሚያወጡትን የተሳሳተ መረጃ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እና ማኅበራዊ ሚዲያ
በማክሸፍ ለሀገራቸው አምባሳደር የኾኑ ኢትዮጵያውያን ተስተውለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ መሐመድ አል አሩሲ ተጠቃሽ ነው፡፡
በሳዑዲ መካ እንደተወለደ የሚነገረው መሐመድ አል አሩሲ ከ300 ጊዜ በላይ በአረብ ሚዲያ በተለይም በአልጀዚራ የቴሌቪዥን
ጣቢያ በመቅረብ ግብጽ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የምታራምደውን የተሳሳተ ዕይታ በአረበኛ ቋንቋ ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ
ያስረዳ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ መሐመድ አል አሩሲ ይህንን ያደረገው የመንግሥት አምባሳደር በመሆኑ ሳይኾን ለሀገሩ ካለው ፍቅር
እንደኾነ ገልጿል፡፡
መሐመድ አል አሩሲ እንዳለው ግብፆች ስለ ዓባይ ለሕዝባቸው እና ለአረቡ ዓለም የተሳሳተ መረጃ ያቀርባሉ፡፡ ይህንን የተሳሳተ
መረጃ ለመቀልበስ በመንግሥት የተመደበ አምባሳደር ሥራ ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያዊ መኾን ብቻ በቂ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ ያላት እንደኾነች የገለጸው መሐመድ አል አሩሲ በእስልምና ሃይማኖትም ትልቅ ቦታ ያላት የቃል ኪዳን ሀገር
መሆኗን አንስቷል፡፡
‹‹ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በምከራከርበት ወቅት ከሌላ ሀገር መጥቶ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለም ይላሉ፤ እኔ ግን የምከራከረው
ኢትዮጵያዊ ኾኜ የሀገሬን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው›› ሲልም ተደምጧል፡፡
‹‹ኢትዮጵያውን ለጎረቤት ሀገሮች ሰላም፣ ብልጽግና እና ዕድገትን እንጅ ምቀኝነትን አንመኝም፤ እኛ የዓባይ ልጆች አንድ ሕዝቦች
ነን›› ብሏል፡፡
መሐመድ አልአሩሲ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሚከራከርበት ወቅት ‹‹የግብጽ ወንድሞቻችን›› የሚለውን ቃል እንደሚጠቀም
አንስቷል፡፡ ይህም የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ዓባይ ያስተሳሰራቸው የዓባይ ልጆች መሆናቸውን እና በጋራ መልማት እንደሚገባቸው
ለማሳየት እንደሆነ ለአልጀዚራ እና ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው ቃለ መጠይቅ አንስቷል፡፡
ሁሉም በተሰማራበት ለሀገሩ አምባሳደር በመሆን መሥራት ይገባል፡፡
በዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleከምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል አባል ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶች በእንጦጦ ፓርክ ችግኝ ተከሉ።
Next articleየኢትዮ – ሩሲያ 11ኛው ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብር የጋራ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡