ቡሩንዲ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተጠቃሚ ለመሆን የታላቁ ህዳሴ ግድብን መጠናቀቅ እየጠበቀች መሆኑ ተገለጸ።

133
ቡሩንዲ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተጠቃሚ ለመሆን የታላቁ ህዳሴ ግድብን መጠናቀቅ እየጠበቀች መሆኑ ተገለጸ።
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዩጋንዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዓለምፀሐይ መሰረት ከቡሩንዲ ውኃ፣ ኢነርጂ እና ማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ኢብራሂም ኡውዜይ ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሁለትዩሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ዓለምፀሐይ መሰረት የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የግድቡ ግንባታ እና ድርድር ያለበትን ሁኔታ በማስረዳት ግድቡ የሁለተኛ ዙር ሙሌት በተያዘለት የጊዜ ሰለዳ መሰረት የሚከናወን መሆኑንና ይህም በሦስቱ ሀገራት መካከል እ.ኤ.አ 2015 በተደረገው የመርሆች መግለጫ ስምምነት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
የቡሩንዲ ውኃ፣ ኢነርጂ እና ማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ኢብራሂም ኡውዜይ በበኩላቸው ካለ ኃይል አቅርቦት ልማት እና እድገት የማይታሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
የተፋሰሱ ሀገራት የሕዝብ ብዛት ቁጥር እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኤሌክትሪክ አቅርቦትም በተመጣጠነ ሁኔታ ማደግ ያለበት ቢሆንም ይህ በአብዛኛዎቹ ሀገራት መሳካት አለመቻሉን ጠቅሰዋል።
ቡሩንዲ በምሥራቅ አፍሪካ በታላላቅ ሐይቆች ውስጥ ያለች እንዲሁም የናይል ተፋሰሰ አባል ሀገር ብትሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቷ በጣም አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በተሻለ ዋጋና አቅርቦት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሀይል ለመግዛት ቡሩንዲ የግድቡን መጠናቀቅ እየተጠባበቀች እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በመገንባት ለቀጣናው በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የኤሌክትሪክ ኃይል-መር ትስስር መፍጠር ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
አምባሳደር ዓለምፀሐይ የህዳሴ ግድብ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ለሚሰቃዩ ከ65 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን መፍትሔ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ግድቡ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካካል እየተፈጠረ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ከማጠናከር እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከመፍጠር ረገድም ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል በውኃ ልማት፣ በኢነርጂ እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ በትብብር ለመሥራት ውይይት እንደተደረገም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየፌደሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር ተሻሽሎ የወጣውን አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸደቀ።
Next articleከምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል አባል ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶች በእንጦጦ ፓርክ ችግኝ ተከሉ።