በመጠናቀቅ ሂደት ላይ የሚገኘው የጎርፍ ማፋሰሻ ዲች ግንባታ መፍረሱ ለጎርፍ አደጋ ስጋት ዳርጎናል ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

131
በመጠናቀቅ ሂደት ላይ የሚገኘው የጎርፍ ማፋሰሻ ዲች ግንባታ መፍረሱ ለጎርፍ አደጋ ስጋት ዳርጎናል ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውሃ ከተማ በተያዘው በጀት ዓመት የጎርፍ አደጋ ችግርን ለመፍታት በከተማው ውሰጥ በርካታ የዲች ግንባታዎች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ቀጠና 6 በተባለው አካባቢ የተገነባው ዲች በግንባታ በጥራት ችግር በመፈራረሱ በነዋሪዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ስጋት ፈጥሯል ።
የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አበባ አሰፋ ግንባታው በታለመለት ጊዜ አለመጠናቀቁና በጥራት አለመሠራቱ ከባለፈው ዓመት በበለጠ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሚኾኑና ክረምቱ እየጨመረ ሲሄድ ቤታቸውን ሊለቁ እንደሚችሉ ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
ለግንባታው መፍረስ ሳይንሳዊ የአፈር ጥናት አለመደረጉ ብቻም ሳይኾን የሳይት አመራረጥ ችግር እንዳለበት የተናገሩት ሌላው ነዋሪ አቶ ቻላቸው በላይ የዲቹ መፈራረስ ከኅብረተሰቡ የጎርፍ ስጋት በተጨማሪ የኢኮኖሚ ኪሳራን እንዳስከተለ ገልጸዋል።
የገንዳውሃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ይግለጥ አበባው የዲች ግንባታው ሕዳር/2013 ዓ.ም ተጀምሮ ሚያዚያ/2013 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ ውል ተወስዶ ወደ ሥራ ቢገባም በቀጣናው የጸጥታ ስጋት ምክንያት አስፈላጊ ግብዓቶች በተፈለገው ጊዜ ባለመቅረባቸው ግንባታው እንዲጓተት ምክንያት ኾኗል ብለዋል።
የዲዛይን ችግር፣ የባለሙያዎች የክትትል ማነስ ፣ ከሲሚንቶ እጥረት ጋር ተያይዞ ትክክለኛ ምጥጥን አለመደረጉና በተገቢው ሁኔታ ውኃ አለመጠጣቱ ለግንባታው መፈራረስ ምክንያት መኾናቸውን ከንቲባው አስረድተዋል፡፡
የችግሩን ባለቤት ለመለየት በሕግ ደረጃና በዞን ገለልተኛ መሀንዲሶች እየተጣራ ነው ያሉት አቶ ይግለጥ አሁን ላይ ችግሩን ለመፍታት ውኃው የሚፈስበትን አቅጣጫ በመቀየር በአዲስ ዲዛይን ውል ተሰጥቶ ሥራው አየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ግንባታው በቅርብ ቀን ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ የተናገሩት ከንቲባው ማኅበረሰቡ ስጋት ሊገባው እንደማይገባ ጠቁመዋል።
ለግንባታው ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ተበጅቷል። እስካሁን 13 ሚሊየን ብር ለሥራ እንደዋለና የበጀት ምንጩ ከክልሉ መንግሥት፣ ከከተማ አስተዳደሩና ከዓለም ባንክ ድጋፍ እንደተገኘ ከገንዳውሃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ-ከገንዳውሃ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleቺርቤዋ-30-10-2013
Next articleየፌደሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር ተሻሽሎ የወጣውን አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸደቀ።