
ኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ ካሳደረው ተፅዕኖ ለመላቀቅ ከተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሠራች መሆኑን ገለፀች።
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “የዲጂታል ትብብር የኮሮናቫይረስ ተፅዕኖ ለመቋቋምና በዘላቂነት ለማገገም” በሚል ዓለም አቀፉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ሕብረት ያዘጋጀው የበይነ መረብ መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተቋቁሞ ለማገገምና ለማጠናከር ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስለሚጫወተው ሚና ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ትርጉም ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለውጥ ለማምጣት የተዘጋጀ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳውን የዓለም ኢኮኖሚ ለመጠገን የዲጂታል ትብብር እና ጠንካራ የበይነ መረብ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ትብብር መስክ ከዓለም ባንክ፣ ከአውሮፓ ሕብረት፣ ከኢስቶኒያና ከሌሎች ሀገራትና ድርጅቶች ጋርም በትብብት እየሠራች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እየሠራቻቸው ያሉ የማሻሻያ ሥራዎች በበይነ-መረብ ግንኙነት ችግር ተፈትነዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ለመቅረፍ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል።
የዩኒሴፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ፋያዝ ኪንግ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ 1 ነጥብ 6 ቢሊየንን ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳደረገና ይህንን ችግር ለመቅረፍ ትምህርት ቤቶችን ከበይነ መረብ ጋር በማገናኘት ዲጂታል ትምህርት መስጠት ላይ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በመድረኩ የተባበሩት መንግሥታትና የልዩ ልዩ ሀገራት ከፍተኛ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያሳደረው ተፅዕኖና ከተፅዕኖው ለመውጣት የተወሰዱ እርምጃዎች ላይ ውይይት መደረጉን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ