ከ247 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በአንድ ጀንበር ለመትከል መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

329
ከ247 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በአንድ ጀንበር ለመትከል መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በዚህ አመት ከሁለት ቢሊዮን በላይ ችግኞች በ185 ሽህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ እንደ ክልል ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ የዝናብ ሁኔታው ምቹ በኾነባቸው በምዕራብ ጎጃም ደጋማ አካባቢዎች እና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳድር በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ተከላ ተካሂዷል ነው ያሉት፡፡ እስካሁንም ከ18 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ቀን ተብሎ መወሰኑንም ነግረውናል፡፡
በዕለቱ በሁሉም ዞኖች ሥር በሚገኙ ከ160 በላይ ወረዳዎች ተከላው ይካሄዳል፡፡ በ24 ሽህ ሄክታር መሬት ላይ 247 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ ነው ያሉት፡፡ በዕለቱ የሚተከሉ ችግኞች በአጠቃላይ ከሚተከሉተ ሁለት ቢሊዮን ችግኞች 13 በመቶ ያህሉ ይሸፍናል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ተከላው የደን ልማት፣ ጥምር ደን እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብትን በስነ-ህይወታዊ ዘዴ ማከም ተብሎ ይተከላል፡፡
ለደን ልማት እና ለጥምር ደን እርሻ የሚያገለግሉ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እንዲኾን ችግኞች ወደ ሚተከሉበት አካባቢ የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ መሳሪያዎችም መዘጋጀታቸው ነው የተገለጸው፡፡
አቶ እስመለዓለም በ2012 ዓ.ም የተተከሉ ችግኞች የመጽደቅ መጠን 78 በመቶ መኾኑን ነግረውናል፡፡ በተከላ ወቅት ተገቢው ጥንቃቄ መደርግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የክልሉ የደን ሽፋን በ2012 ዓ.ም ከነበረው ከ14 ነጥብ 6 ወደ 15 ነጥብ 3 ማደጉን እና በቀጣይ ወደ 15 ነጥብ 8 ለማሳደግ እየተሠራ እንደኾነ ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኢትዮጵያ መርከብ ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብ መደበኛ የጭነት አገልግሎት መስጠት ጀመረች።
Next articleኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ ካሳደረው ተፅዕኖ ለመላቀቅ ከተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሠራች መሆኑን ገለፀች።