
የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልልና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ ተገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም 6ኛውን ክልላዊና ሀገራዊ ምርጫ አካሂዳለች። ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ችግር በስኬት መካሄዱንም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የ6ኛው ክልላዊና ሀገራዊ ምርጫ የማጠቃለያ ግምገማና የቀጣይ አቅጣጫ የውይይት መድረክ በፍኖተሰላም ከተማ ተካሂዷል።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ብሎም በሕዝቡ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ቀደም ብሎ ሥራ መሠራቱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስሜነህ አያሌው ተናግረዋል።
በዞን ደረጃ የተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ቤት ችግሮችን ለይቶ በመፍታትና አባላትና ደጋፊዎቻቸውም ሰላማዊ የምርጫ ሂደትን እንዲከተሉ በተሠራው ሥራ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል። ከምርጫ በኋላም ሕዝቡ ወደ መደበኛ ሥራው መግባቱን የተናገሩ::
“ማን አሸነፈ ማን ተሸነፈ ሳንል” ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝብ የሠጠንን ድምጽ በማክበር አንድ በሚያደርጉ ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ልናተኩር ይገባልም ብለዋል።
ሴቶች የምርጫ ካርድ በማውጣት ይሆነኛል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ከመምረጥና ከመመረጥ ጀምሮ የተሻለ የምርጫ ሂደት መታየቱን የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ የሻረግ ታፈረ ናቸው።
በምርጫው ወቅትም ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡ ሴቶች ውስጥ ከ63 ነጥብ 3 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ድምጽ የሠጡ ሲሆን ይህም ካለፋት የምርጫ ዓመታት ሴቶች የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን ያደረጉት ፖለቲካዊ ተሳትፎ መሻሻል የታየበት ነው ብለዋል።
“ስልጣንና ፓርቲ ከሕዝብ በታች መሆናቸውን አውቀን ለሀገር ሰላምና አንድነት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅድሚያ ሊሠጡ ይገባል” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዶክተር ማተቤ ታፈረ ናቸው። “አሁን ላይ በሀገራችን ተስፋም ስጋትም ያለበት ወቅት ነው” ያሉት ዶክተር ማተቤ ፓርቲዎች ለሀገር አንድነትን ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ባሉ የምርጫ ክልሎች በዘንድሮው ምርጫ 897 ሺህ 203 የኅብረተሰብ ክፍሎች የምርጫ ካርድ ያወጡ ሲሆን 528ሺህ 666 ደግሞ ድምጽ መስጠታቸው ተጠቅሷል።
ዘጋቢ:–ዘመኑ ይርጋ– ከፍኖተሰላም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ