የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያካሂደውን ስብሰባ በመቃወም ሰልፍ ሊካሄድ ነው።

319

የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያካሂደውን ስብሰባ በመቃወም ሰልፍ ሊካሄድ ነው።
ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው
ምክር ቤት የሚያካሄደውን ስብሰባ በመቃወም በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በኒውዮርክ ሰላማዊ ሰልፍ
ሊያደርጉ መሆኑ ተገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ግብጽ ባቀረበችው ጥያቄ
መሰረት ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም ስብሰባ ያደርጋል።
በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት
ተገኝተው የጸጥታው ምክር ቤት በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚያደርገውን ስብሰባ ይቃወማሉ።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ስብሰባውን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በዋሺንግተን ዲሲ
የሰላምና አንድነት ግብረ ኃይል ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ጣሰው መልዓከ ሕይወት ለኢዜአ ገልጸዋል።
“የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው። ግድቡን አስመልክቶ የአረብ ሊግና የተባበሩት መንግሥታት
ድርጅት ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የለውም፤ ይህንንም እንቃወማለን” ብለዋል አስተባባሪው።
የሦስትዮሽ ውይይቱ በአፍሪካ ሕብረት አዳራዳሪነት መቀጠልና መፍትሔ ማግኘት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ከዚህም አኳያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በግድቡ ዙሪያ የሚያደርገው ስብሰባ ተቀባይነት የሌለው
በመሆኑ ዳያስፖራዎች ስብሰባውን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፉን እንደሚያከናውኑ አመልክተዋል።
የሰልፈኞቹ ተወካዮች በስብሰባው ላይ ለሚሳተፉ ዲፕሎማቶችና በተመድ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች የተቃውሞውን መልዕክቶች
የሚገልጽ ደብዳቤ እንደሚያስገቡና በራሪ ወረቀቶችን እንደሚሰጡም ገልጸዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርሲ፣ ቦስተን፣ ኮኔክቲከት፣ ቨርጂኒያ፣ ዴልዌር፣ ፔንሲልቫኒያ ፣ ዋሺንግተን ዲሲ፣
ሜሪላንድና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየደረሰባት ያለውን ጫና በመቃወምና በመመከት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ለሀገሩ
አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝና የሐሙሱ ሰልፍም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ሰልፉን በዋሺንግተን ዲሲ የሰላምና አንድነት ግብረ ኃይል ኢትዮጵያ፣ በኒው ዮርክ ከተማ የሚገኘው ተስፋ በኢትዮጵያ ቡድን
አባላትና ሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እንዳስተባበሩት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት ጊዜያዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዓለማየሁ ስለሺ ፤ በአሜሪካ የሚኖሩ
ዳያስፖራዎች የፊታችን ሐሙስ በሚካሄደው ሰልፍ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዳያስፖራው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብ፣ በጉልበትና በእውቀት የሚያደርገውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ
ይቀጥላልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ፤ ግብጽና ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድርን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት
ተቀባይነት የሌለው መሆኑንና በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት የሚካሄደው ድርድር መፍትሔ ያመጣል ብላ እንደምታምን በተደጋጋሚ
ጊዜ ስትገልጽ ቆይታለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት
ትናንት በጻፉት ደብዳቤ የአረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያ
እንደማትቀበለውና እንደምታቀወመው መግለጻቸው ይታወሳል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበደቡብ ሱዳን ቦር የሚገኘው የ14ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የተባበሩት መንግሥታትን የሰላም ማስከበር ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነ።
Next articleየፖለቲካ ፓርቲዎች በክልልና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ ተገለጸ።