
በግብር ዘመኑ ከእቅዱ 85 በመቶ ገቢ መሰብሰቡን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1/2013 ዓ.ም ጀምሮ ግብራቸውን እንዲከፍሉ መምሪያው አሳሰቧል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ገቢዎች መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደሴ ጥሩነህ እንዳሉት ከሐምሌ 1/2013 ዓ.ም ጀምሮ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳድሮች በ10 ቀናት ውስጥ ከፍለው እንዲያጠናቅቁ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
ከባለድርሻ አካላት ጋር በዞን ደረጃና በወረዳ ደረጃ ሰፊ የመግባባት ሥራ እየተሠራ እንደኾነ የተናገሩት አቶ ደሴ ግብር ከፋዮችን ለማስተናገድ ተገቢ ዝግጅት እየተደረገና የቅስቀሳ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ መምሪያው በ16 ወረዳዎች ተግባሩን የሚደግፍ የባለሙያዎች ቡድን እንደሚልክም ነው የተናገሩት፡፡
አቶ ደሴ እንደነገሩን በ2013 በጀት ዓመት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከ777 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር ለመሰብሰብ አቅዶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም 621 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡ የእቅዱን 85 በመቶ መሰብሰብ የቻለው ዞኑ በቀሪ ቀናት ወደ 95 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ነው የገለጸው፡፡
እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት በቀጠናው የነበረው የፀጥታ ችግር እንቅፋት እንደነበር የመምሪያው ኀላፊ ነግረውናል፡፡
ለተጀመሩ ልማቶች መሳካትና ለአካባቢው ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ ሁሉም ግብር ከፋይ በተያዘው ቀነ ገደብ የሚጠበቅበትን ግብር እንዲከፍል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከ17 ሺህ በላይ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች እንዳሉ ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡-ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ-ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ