
በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል እየተሠራ እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል እና ጉዳቱን መቀነስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በደሴ ከተማ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡
በዚህ ዓመት የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከሌላው ጊዜ የተለየ በመሆኑ የመከላከል ሥራውን ከሌላው ጊዜ በተለየ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል አራት ዞኖች ማለትም በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋና ሰሜን ወሎ እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የተከሰተው የበረሃ አንበጣ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም ጉዳቱን ለመቀነስ ግን ሳይቻል ቀርቷል፡፡
በዚህ ዓመት ደግሞ የአንበጣ መንጋው ከሌላው ጊዜ በተለየና ባልተለመደ መልኩ በክረምቱ መግቢያ ላይ ጀምሯል፡፡ በሰብል፣ በመኖና በደን ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡
ከሰኔ 22/2013 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ወሎ ዞን የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ እስካሁንም በዞኑ ሰባት ወረዳዎች በሚገኙ 60 ቀበሌዎች 9 ሺህ ሄክታር መሬት በመውረር 3 በመቶ ያህል ሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ መንጋው የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ እንዳይሆንም ከወዲሁ የመከላከል ሥራውን ለማጠናከር እየተሠራ ይገኛል፡፡
በ2013/14 የምርት ዘመን በአማራ ክልል ከ130 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በምርት ዘመኑ የበረሃ አንበጣ መንጋ መከሰቱ ትልቅ ስጋት መፍጠሩን ነው የክልሉ ግብርና ቢሮ የገለጸው፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ባለው ውይይት ላይ የመነሻ ፅሁፍ ባቀረቡበት ወቅት ዘንድሮ ሰፊ ምርት ለመሰብሰብ አቅደን እየሠራን ቢሆንም ቀድሞ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እቅዱ እንዳይሳካ እንቅፋት ይፈጥርብናል ብለዋል፡፡
የበረሃ አንበጣ መንጋ ብዙ ጊዜ የሚከሰተው ከክረምቱ በኋላ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ በዚህ ዓመት ግን ከሌላው ጊዜ በተለየና ባልተለመደ ሁኔታ በክረምቱ መግቢያ ላይ መከሰቱ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ የመከላከል ሥራውም በተለየ ትኩረት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አሊ ይመር – ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ