ኢትዮጵያ የርሃብ መድኃኒቷን፣ የመታረዝ እራፊዋን ዛሬ ትሸኛለች፡፡

97
ኢትዮጵያ የርሃብ መድኃኒቷን፣ የመታረዝ እራፊዋን ዛሬ ትሸኛለች፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ግማሽ ምዕተ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ በእናትነት የዘለቁት በጎ አድራጊ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መሥራች፣ አዛኝ እናት ክብርት ዶክተር አበበች ጉበና “አፈሩ ይቅለልዎት” ሊባሉ ግድ ሆነ፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ የርሃብ መድኃኒቷን፣ የመታረዝ እራፊዋን እና ገመና ሸሻጊዋን ትሸኛለች፡፡ በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እናትና እመቤት፣ መጠጊያና መጠለያ፣ አምባና መሸሸጊያ ሆነው ዘመናቸውን ሁሉ አሳልፈዋል፡፡
ትዳራቸውን ትተው፣ ራሳቸውን ረስተው እና ያላቸውን ሀብትና ንብረት አጥተው በሕይዎት ዘመናቸው ሁሉ ሰው ብቻ አፍርተዋል፡፡
ከጣሊያን ወረራ አንድ ዓመት በኋላ በ1929 ዓ.ም እንደተወለዱ እና አርበኛ አባታቸው በጣሊያን ጦርነት ውጊያ ላይ እንዳሉ ሕይዎታቸው ማለፉን ተከትሎ ክብርት ዶክተር አበበች ጉበና እድገታቸው ሁሉ ከእናታቸው ጋር ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ ከተወለዱበትና ካደጉበት ከሰላሌ ሸበል የአለድሜ ጋብቻን ለማምለጥ ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም ኑኖአቸውን በዜው አደረጉ፡፡
ዓለም የሚያውቀውን ርህራሄ እና የብዙኀን እናትነት አጋጣሚ የሚፈጥር አንድ ጉዞ ደግሞ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ አደረጉ፡፡ በወቅቱ መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለመደበቅ የሚታገለውን እና የበርካቶችን ሕይዎት የቀጠፈውን የርሃብ አደጋ በአይናቸው አዩ፡፡ ወላጆቻቸው በሞት ያጡ ሁለት ህጻናትን አንድ ከሐይቅ አንድ ደግሞ ከግሸን አካባቢ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡
ወደ አዲስ አበባ ስመለስ “የወትሮዋን አበበች መሆን አልቻልኩም” ይሉ የነበሩት እናት ዘመናቸውን ሁሉ ለበጎ አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ ያዩት ያ መከራ እና ስቃይ አስገደዳቸው፡፡ ሥራ እና ሕይዎት፣ ትዳር እና ቤት ለዚች እናት ትርጉም አልባ ልማድ ሆኑባቸው፡፡ በርሃቡ ምክንያት አቅም አግኝተው እና ከሞት ተርፈው አዲስ አበባ የገቡ ወገኖች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ወድቀው መታየት ጀመሩ፡፡ ይህንን እያዩ ማለፍ ያቃታቸው እናት አበበች 20 የሚደርሱ ህጻናትን ከየጎዳናው አሰባስበው ወደ ቤታቸው በመውሰዳቸው ትዳራቸው ሳንካ ገጠመው፡፡ ድርጊታቸውን የደገፈ እና ከጎናቸው የቆመ ማንም አልነበረም፡፡ ኑሯቸው ተመሰቃቀለ፡፡ አማራጭ ያሉት ብቸኛው መንገድ ዶሮ በሚያረቡበት አንድ ጫካ አካባቢ ህጻናቱን ይዞ መቀመጥ ነበርና እርሱን አደረጉት፡፡
አካባቢው የጅቦች መተራመሻ ቢሆንም ለዚህች እናት ጅቦች ሳይቀር የራሩላቸው ይመስል አካባቢውን በመልቀቃቸው እናት አበበች ከህጻናቱ ጋር ድህነት ያጠላበትን ሰላማዊ ኑሮ ቀጠሉ፡፡ የእናት አበበችን ተግባር የሰሙና የተቸገሩ ወላጆችም ልጆቻቸውን እያመጡ እንዲያሳድጉላቸው ይሰጧቸው ነበር፡፡ ፖሊስ ሳይቀር ጎዳና ላይ ያገኛቸውን ህጻናት እያሰባሰበ ወደ እናት አበበች ጉበና ይወስዳቸው ነበር፡፡
በሂደት የተወሰኑ የእርዳታ ድርጅቶች የተወሰነ የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ክብርት አበበች ግን ከእርዳታ ይልቅ በሥራ ላይ የተመሰረተ የገቢ ማግኛ ዘዴን ምርጫቸው አደረጉ፡፡ ይህም ለህጻናቱ የቀጣይ ህይዎት መስመር መስተካከል ሲባል የመጣ ፍላጎት ነበር፤ እርዳታ በህጻናቱ አዕምሮ ውስጥ በቅሎ እንዲያድግ አልፈለጉም፡፡ እንጀራ እየጋገሩ ለሆቴሎች እና ድርጅቶች ከማቅረብ ጀምሮ ያልተሞከረ የገቢ ማግኛ ዘዴ እንዳልነበርም በሕይወት እያሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
በ1979 ዓ.ም አካባቢ የህጻናት ማሳደጊያ ድርጅት አቋቁመው ህጋዊ እውቅናም አገኙ፡፡ በአራተኛ ዓመቱም መንግሥት ለእርሻ አገልግሎት የሚውል ሰፊ መሬት ሰጣቸው፡፡ ምርት ማምረትን እና እንስሳትን ማራባት በሰፊው ቀጠሉበት፡፡
እናት አበበች ህጻናቱን ወደ ማሳደጊያ ማዕከላት የሚያመጡት ሁሉንም አማራጮች ሞክረው ካልተሳካ በቀር ነበር፡፡ ከጎዳና አንስተው፣ ከሞት መንጋጋ ፈልቅቀው እና አሳድገው ለደረጃ ያበቋቸው ልጆቻቸው እጅግ በርካቶች ናቸው ይባላል፡፡ እርሳቸውም የደስታ ምንጫቸው ህጻናቱ አድገው እና የተሻለ የሕይዎት ደረጃ ላይ ደርሰው ለማኅበረሰቡ ትርጉም ያለው አበርክቶ ሲኖራቸው ማየታቸው እንደነበርም ይነገራል፡፡
በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ አካባቢ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት እና የህጻናት መሳደጊያዎችን አቋቁመው በርካቶችን ከከፋ የሕይዎት ውጣ ውረድ የታደጉት እናት ምድራዊ ተልዕኳቸውን በሚገባ አጠናቀው ይሕችን ምድር ተሰናብተዋል፡፡ ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢም በቅድስት ስላሴ ካቴደራል ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል፡፡
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም ለክብርት ዶክተር አበበች ጉበና ወዳጅ ዘመድ፣ ለልጆቻቸው እና ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ መጽናናትን ይመኛል፡፡ የመረጃ ምንጭ፡- “ጽናት” የ100 ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ተሞክሮ መጽሄት
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ውጤታማ መሆናቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የገለጎ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
Next articleክልሉን ከማናቸውም ጥቃት ለመመከት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ፡፡