በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ውጤታማ መሆናቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የገለጎ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

144
በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ውጤታማ መሆናቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የገለጎ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 29/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገለጎ ከተማ በቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ወጣት ማንደፍሮ እሸቴ የገለጎ ከተማ ነዋሪ ነው። በተፈጠረለት የሥራ ዕድል በማኒፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፍ ተሰማርቶ እየሠራ ይገኛል። በሥራውም ውጤታማ በመሆን የሎጅ ባለቤት ሆኗል።
በዳቦ ጋጋሪነት፣ በመስተንግዶ፣ በጥበቃና በሌሎች የሥራ ዘርፎች በሥሩ ለ14 ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ለሠራተኞችም በወር ከ38 ሺህ ብር በላይ ደሞዝ እንደሚከፍል ተናግሯል።
ሠርቶ ለመለወጥ መሠረቱ የዓላማ ጽናት ነው ያለው ወጣት ማንደፍሮ ማንም ከትንሽ ነገር ተነስቶ ራሱን መለወጥና ኑሮን መቀየር ይችላል ብሏል።
በዳቦ ጋጋሪነት የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ጌታቸው ታደሰ ከሥራ አጥነት በመውጣት በሚከፈለው የወር ደሞዝ ቤተሰቡን እንደሚመራ ተናግሯል።
ሌላኛዋ ወጣት ቤዛ ኤፍሬም “ከአሁን በፊት ሥራ በማጣቴ ህይወቴን ለመምራት ተቸግሬ ነበር፤ አሁን ግን ከራሴ አልፎ ቤተሰቦቼንም ለማገዝ ችያለሁ” ብላለች።
ከ700 መቶ ብር ተነስቶ 2 ሚሊዮን ብር ካፒታል የደረሰው ወጣት ማንደፍሮ ካፒታሉን ለማሳደግና ለሌሎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዝግጁ ቢሆንም የብድር አገልግሎትና ተጨማሪ የመሸጫ ቦታ ባለማግኘቱ መቸገሩን ተናግሯል።
የወጣቶችን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንሠራለን የሉት የቋራ ወረዳ ቴክኒክና ሙያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታከለ ሰይፉ የብድር አገልግሎት ያልሰጠንበት ዋና ምክንያት ወጣቱ የወሰደውን ብድር በስዓቱ መመለስ ባለመቻሉ ነው ብለዋል።
አቶ ታከለ አክለውም በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁና ለሚደራጁ ወጣቶች ቦታ ለመስጠትና ብድሩን ለማስመለስ ወረዳው ግበረ ኀይል አቋቁሞ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በወረዳው 644 ኢንተርፕርይዞች እንደሚገኙና ለ1 ሺህ 448 ወጣቶች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፈጠሩም ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ– ከቋራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየክብርት ዶክተር አበበች ጎበና አስክሬን ሽኝት መርኃግብር እየተከናወነ ነው፡፡
Next articleኢትዮጵያ የርሃብ መድኃኒቷን፣ የመታረዝ እራፊዋን ዛሬ ትሸኛለች፡፡