
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ለማግኘት ለተደራጁ ማኅበራት የተገለጸው የካሣ ክፍያ የተሻሻለውን የካሣ አከፋፈል መመሪያ መሠረት ያደረገ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ለማግኘት የተደራጁ ማኅበራት የካሣ አከፋፈልን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫዉን በጋራ የሰጡት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን እና የከተማ አስተዳደሩ ግብርናና ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መምሪያ ናቸው።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ግብርናና ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መምሪያ ኀላፊ ትልቅሰው እምባቆም ማኅበራት ለአርሶአደሮች የተዘጋጀውን ካሣ ገቢ እያደረጉ ነው ብለዋል። የመኖሪያ ቤት ቦታን ለማግኘት ተደራጅተው ሲጠባበቁ የነበሩ ማኅበራት ካሣው በዝቶናል በማለት ጥያቄ ማንሳታቸውን ተናግረዋል።
ካሣው ሊጨምር የቻለው ካሁን ቀደም ሲሠራበት በነበረው መመሪያ በተለየ አዲስ መመሪያ፣ አዋጅና ደንብ በመውጣቱ ነው ብለዋል። ነባሩ መመሪያ ቁጥር 7/2010 ተሽሮ በመመሪያ ቁጥር 44/2013 ተተክቷል ብለዋል።
“በመመሪያ ቁጥር 7/2010 መሠረት አርሶአደሮች ከይዞታቸው ሲነሱ መሬታቸው ያፈራውን ሀብትና ንብረት የለቀቁበት ካሣ የሚባዛው በ10 ዓመት ነበር። አዲሱ መመሪያ ቁጥር 44/2013 ደግሞ አርሶአደሮች ከመሬታቸው በዘላቂነት በሚነሱበት ወቅት መሬታቸው ያፈራውን ሀብትና ንብረት ካሣ የሚባዛው በ15 ዓመት ሆኗል” ብለዋል። መሬቱ የአትክልት፣ ሰብልና የእርሻ ላይ ሃብትን ኹሉ በማካተት በባለሙያዎች መረጃ እየተያዘ ካሣው የሚሰላ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ኀላፊው በሰጡት መግለጫ ነባሩና አዲሱ የካሣ ስሌት የጎላ ልዩነትን ይፈጥራል። የበፊቱ መመሪያ የሰብልን ተረፈ ምርት ግምት ውስጥ አያስገባም ነበር ያሉት አቶ ትልቅሰው አዲሱ መመሪያ ግን ከምርቱ የሚገኘውን ተረፈ ምርት ሳይቀር መረጃው ተባዝቶ በ15 ዓመት የሚሰላ መኾኑን አስረድተዋል።
የሃብት ዋጋ ትመናው ሥራ አርሶአደሮች፣ የገጠር መሬት አስተዳደር ግብረኃይል፣ የቀበሌ አመራር፣ የጸጥታ ኀይል ባሉበት የሚሰላ መኾኑን ኀላፊው ያስገነዘቡት። ከመጀመሪያ ጀምሮ ለማኅበራት አባላትም ኾነ ለአርሶአደሮች በቂ ግንዛቤ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በዘንዘልማ ሳይት 442 በሄክታር መሬት የተካለለ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ትልቅሰው የካሣ ስሌቱም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ አካባቢም በፍተኛ የአትክልትና ፍራፍሬ የተሸፈነ በመሆኑ ካሣው ሊጨምር እንደሚችል ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ብለዋል። “በዘንዘልማ ለተደራጁ ማኅበራትም ሒሳቡ ተጠናቅቆ ለማፀደቅ ወደሚመለከተው ክፍል ገብቷል” ብለዋል።
ማኅበራት ካሣው ሲገለጽ ለአርሶ አደሮች ካሳውን በፍጥነት ማስገባት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የመሬት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ታረቀኝ የኋላ ከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ቦታ ችግርን ለመፍታት ከአርሶ አደሮች ጋር በተደጋጋሚ ምክክር ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል። ይህም ረጅም ጊዜን እንደወሰደባቸው ጠቁመዋል።
የካሳው ስሌት በጥናት ላይ የተመሠረተ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታረቀኝ “በመሸንቲ ሳይት ለተደራጁ ማኅበራት የተገለጸው የካሣ ስሌት ግልጽና ኹሉም ሰው ሊተች በሚችልበት ሁኔታ የቀረበ ነው” ብለዋል። በመሸንቲ ሳይት የተደራጁ የቤት ማኅበራት ለከተማዋ እድገት የጎላ ጠቀሜታን ይሰጣል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ