የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት አሳሳቢ እንደኾነበት የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

290
የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት አሳሳቢ እንደኾነበት የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ በኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሶሶ ላይ በተፈጸመ ስርቆት በተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ አጋጥሟል፡፡ ከባሕር ዳር-ወረታ በተዘረጋ 66 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሶሶ ላይ በደረሰ ስርቆት ከወረታ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ኀይል የሚያገኙ አካባቢዎች ለችግር ተጋልጠዋል፡፡
በዚህም ወረታ፣ አዲስ ዘመን፣ እብናት፣ አምበሳሜ እንዲሁም በአቅራቢያቸው የሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኀይል ተቋርጦባቸዋል ተብሏል፡፡
የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆትና ውድመት ክልሉን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው እንደሆነ የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በተለይ በምዕራብ አማራ አካባቢዎች በብረት ምሶሶና በኤሌክትሪክ አስተላላፊ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ስርቆት እየተባባሰ መኾኑን የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰለሞን ጣሰው ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትን ሰርቆ መሸጥ፣ የክልሉን ሕዝብ ረፍት መንሳትና ማበሳጨት የስርቆቱ ዓላማ ሊኾን እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡ ድርጊቱ ደንበኞችን ለእንግልት፣ መንግሥትንም ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገ አንደኾነ ነው አቶ ሰለሞን የገለጹት፡፡
ትኩረት ሰጥቶ በባለቤትነት ድርጊቱን አለማስቆም ችግሩ እንዲባባስ አድርገውታል፡፡ ከዚህ ቀደም ችግሩን ፈጽመው በተገኙ አካት ላይ አስተማሪ ርምጃ አለመወሰዱም ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ተነስቷል፡፡
የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን በመንግሥት ጥበቃ ብቻ መታደግ ስለማይቻል ማኅበረሰቡ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ፣ መሠረተ ልማቱን የሚነካኩ አካላትን ማንነት መጠየቅ፣ የተቋሙ ሠራተኞች መኾናቸውን ማረጋገጥና ድርጊቱን የሚፈጽሙ ካሉ ለሕግ አካላት እንዲጠቁሙ አቶ ሰለሞን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች በማስተካከል ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡
አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር ድረስ ደንበኞች በትዕግስት እንዲጠብቁም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ለራስ ሳይሆኑ ስለሌሎች መኖር”
Next articleየባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ለማግኘት ለተደራጁ ማኅበራት የተገለጸው የካሣ ክፍያ የተሻሻለውን የካሣ አከፋፈል መመሪያ መሠረት ያደረገ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡