
“ለራስ ሳይሆኑ ስለሌሎች መኖር”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በ1928 ዓ.ም አካባቢ በሰሜን ሸዋ ሰላሌ አውራጃ ልዩ ስሙ ሸበል በሚባል አነስተኛ መንደር ተወለዱ፤ የጣሊያንን ወረራ ለመከላከል የዘመቱት አባታቸው በጣሊያኖች ስለተገደሉባቸው አያታቸው ጋር አደጉ፤ ዘጠኝ ዓመት ሲሞላቸው እናታቸው የአሳዳጊነት ኃላፊነትን አስፈረዱ እና ለሦስት ዓመት ወላጅ እናታቸው ጋር ቆዩ ፤ በአካባቢው ወግ መሠረት በልጅነታቸው ለትዳር ቢታጩም ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ጋብቻ ሳይፈጽሙ ቀሩ፡፡
አዲስ አበባ እንደደረሱ የሚያውቁትም ኾነ የሚገቡበት ቦታ አልነበራቸው፤ የጉምሩክ ባለስልጣን መሥሪያ ቤት በር አካባቢ ተቀምጠው ያገኟቸው የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስተዳዳሪ ወሬያቸውን ሠምተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ወስደው የቤተሠቡ አባል አደረጓቸው፡፡
ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና በአሳዳጊዎቻቸው ቤት ውስጥ የእጅ ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ በኋላም በተለያዩ ፋብሪካዎች ተቀጥረው ሠርተዋል፡፡ በሥራቸው ውጤታማ በመሆናቸው በአንድ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ የጥራት ተቆጣጣሪ ኾኑ፡፡ በዚያም ትዳር መሠረቱ፡፡ ወደ ግሼን ማርያም የሚወስደውን መንገድ ለማሠራት በተቋቋመው ገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው ሠርተዋል፡፡ በዚህ ወቅት በተፈጠረላቸው እድል ወደ ግሼን ማርያም አቀኑ፤ በወቅቱ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ድርቅ ባስከተለው ረሀብ በርካቶች አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ተሻለው አካባቢ ቢጓዙም ካሰቡት ሳይደርሱ የረሀቡ ጠኔ በመንገድ አስቀርቷቸዋል፡፡ ወይዘሮ አበበች በተመለከቱት ነገር ልባቸው ቢሰበርም የረሀቡ ጠኔ ነፍሳቸውን ከቀማቸው ወላጆች አጠገብ ያገኟቸውን ሁለት ሕጻናት ይዘው ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥም ከቤተሰቦቻቸው የተቀበሏቸው ሕጻናት ቁጥር 20 ደረሰ፡፡
ትዳራቸውን እና ሥራቸውን አቋርጠው ልጆችን ይዘው ዶሮ በማርባት ወደ ሚተዳደሩበት ቦታ አመሩ፡፡ ቦታው ምቹ ባይሆንም እሳቸው ባደረጉት ጥረት ቦታው ለሕጻናቱ ምቹ ሆኖ ነበር፡፡ ዜናው በየአካባቢው በመዳረሱ በርካታ እናቶች ልጆቻቸውን እያመጡ ይሰጧቸው ነበር፡፡ በተጨማሪ ፖሊስ በየቦታው ተጥለው የሚያገኛቸውን ሕጻናት ያመጣ ስለነበር የሕጻናቱ ቁጥር 40 ደረሰ፡፡ ቀስ በቀስ በጎ አድራጊ ድርጅቶች እና ግለሠቦች እርዳታ ይሠጧቸው ጀመር፡፡
የካቶሊክ ተራድኦ አገልግሎት እና የጀርመኑ “ሜንሽን ፎር ሜንሽን” ወይም ሰዎች ለሰዎች የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ለሕጻናቱ ምግብ ካቀረቡላቸው ድርጅቶች የመጀመሪያው ነበር፡፡ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅትም ስንዴ አቀረበላቸው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት እና ትምህርት ተራድኦ አንድ የልብስ ስፌት ማሽን አቀረበላቸው፤ ሁለት የመሥሪያ ክፍልም ገነባላቸው፡፡
መንግሥት በሠጣቸው ሠፊ ቦታ ላይ መኝታ ቤት፣ የስልጠና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት እና ሆስፒታል ለመገንባት ከበርካታ ምንጮች ድጋፍ አገኙ፡፡ ድርጅታቸው ሕጋዊ ሰውነት ባገኘ በአራት ዓመቱ በ1983 ዓ.ም ከመንግሥት ባገኙት ቦታ የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት እና እንስሳትን በማርባት የራሳቸውን የዓመት ገቢ መሸፈን ጀመሩ፡፡
ወይዘሮ አበበች ሕጻናትን ከማሳደግ በተጨማሪ እናቶች አቅማቸው ጎልብቶ ልጆቻቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳደሩ ለማድረግም ሠፊ ጥረት አድርገዋል፡፡
በአንድ ወቅት ”ሕጻናትን ወደ ማሳደጊያ አምጥተን የምናሳድግ ሌላ ምርጫ ከጠፋ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ “ከሁሉም በላይ ትልቅ ደስታ የሚሠማኝ የማሳድጋቸው ልጆች ለወግ እና ለማዕረግ በቅተው ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ሆነው ስመለከት ነው “ብለው ተናግረው ነበር በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ፡፡
እንደዚህ የተጀመረው መልካምነት ቀጥሎ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ከ12 ሺህ በላይ ሕጻናትን ይረዳሉ። በእሳቸው የእርዳታ ድርጅት ሥር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ይነገራል። በዚህ ሥራቸው ከጅማ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት አግኝተዋል፡፡
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራች እና አስተባባሪ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሆነው በሠሩት ሥራ ስማቸው ከመቃብር በላይ ይውላል ብለዋል፡፡
ሲስተር ዘቢደር የጀመርሁት የሕጻናት ማሳደጊያ አሁን ባለበት ደረጃ እንዲደርስ ከረዱኝ ሠዎች መካከል ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ቀዳሚዋ ናቸው ብለዋል፡፡ ባገኘሁት ልምድ፣ ባየሁት የእናትነት ፍቅር ተስቤ የሕጻናት ማሳደጊያ ለመክፈት ችያለሁ ነው ያሉት፡፡
ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ሌሎች ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች በሌሉበት የጀመሩት ሥራ ብዙ ሕጻናትን ከሞት እና ከረሀብ ታድጓል ነው ያሉት ሲስተር ዘቢደር፡፡
ክብርት ዶክተር አበበች ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያም ካካፈሉት ትልቁ ልምድ አንዱ ልጆችን ለውጭ ሀገር ጉዲፍቻ ከመላክ ይልቅ በሀገራቸው ማደግ እንዳለባቸው ነው ብለዋል፡፡
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የሕጻናት አስተዳደግ ባገኘነው ተሞክሮ ወደ ሥራ ገብተን ውጤታማ ሆነናል ነው ያሉት፡፡
ሲስተር ዘቢደር በክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ህልፈተ ህይወት የተሠማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል፤ የእሳቸውን ራዕይ መንግሥት፣ ያሳደጓቸው ልጆች እና ማኅበረሰቡ እንዲያስቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና በቅርቡ በኮሮና ህመም ምክንያት በጳውሎስ ሆስፒታል ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 27/2013 ዓ.ም በተወለዱ በ85 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል፡፡
ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ በክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ህልፈተ ህይወት የተሰማቸው ሐዘን በገለጹበት ወቅት ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና የጀመሩት መልካም ሥራ ለአፍታም እንደማይቋረጥ በራሳቸው እና በከተማ አስተዳደሩ ስም ቃል ገብተዋል፡፡
በትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ