
“ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይቻልም፤ ለብዙ ኃይሎች ይህን ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ወቅታዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮችን ዳስሰዋል፡፡
የአንዳንድ ሀገራት ብዙኃን መገናኛ ተቋማት የመንግሥትን ጥረት እና በጎ ሥራዎች እንደላዩ አልፈው መከላከያ ከትግራይ ሲወጣ በብዙ መንገድ እያራገቡ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆም ብሎ ጉዳዩን ሊመረምር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ አሁን ያለውን የኢትዮጵያን መንግሥት ለመቀየር የሚያስቡ ሀገራት ስለ መኖራቸው መረጃዎች አሉን ያሉት ጠቅይ ሚኒስትሩ ሀገር እስከቀጠለች ድረስ መሰረታዊ ችግራችን ስልጣኑ አይደለም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት በተደጋጋሚ የግምገማ ችግር ነበረበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጤቱን ሕዝቡ እንዲገመግመው መተው ይገባል ነው ያሉት፡፡
“ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይቻልም፣ ለብዙ ኃይሎች ይህንን ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋልም” ብለዋል፡፡
ለመከላከያ ተቋሙ የተመደበው በጀት በቂ ባይሆንም ከባለፈው የተሻለ በጀት ተመድቧል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ወታደር ያለውን ልብ ማንም የለውም ብለዋል፡፡ ስለ ጀግንነቱ ስላየሁት መናገር እችላለሁ፣ ጀግና ነው ተራራን ይወጣል ይወርዳል፣ በዝናብ በጸሐይ ይጓዛል፣ ለሀገሩ ክብር ይሞታል፣ የእኛ ዘመናዊ ትጥቅ ልባችን ነው፣ ይሄ የማይታበል፣ በተግባር የታዬ እና ወደፊትም የሚታይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
መካለከያ ብዙ ሃብት የለውም፣ ብዙ ልብና ብዙ ህልም አለው፣ ሀገሩን ይወዳል፣ መከላከያውን የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤ ሕዝቡም መከላከያ ማለት ሀገር ማለት እንደሆነ ገብቶት በሞራል እየደገፈው ነው፣ የሕዝቡ ፍቅርና ሞራል ይጠብቀዋል ብለዋል፡፡
መከላከያውን በሞራል፣ በስንቅና በትጥቅ ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያን መታደግ የሚቻለው ጠንካራ ሠራዊት ስንገነባ መሆኑን በማወቅ ወጣቶች አዋጅ ሳይጠብቁ ሠራዊቱን መቀላቀል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ የተበጀተው በጀት የምንፈልገውን ሥራ ያሠራናል፣ ከምንፈልገው በላይ የሚመጣ ካለ ደግሞ ለምክር ቤቱ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ