የኢምባሲዎችን እና የዲፕሎማቶችን ቁጥር መቀነስ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

197
የኢምባሲዎችን እና የዲፕሎማቶችን ቁጥር መቀነስ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ቀዳሚ ከሚባሉ የዓለም ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ሕብረት መስራች አባል ሀገርም ነች፡፡
በተለያዩ ሀገራት ኢምባሲዎችንና ቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶችን አቋቁማ ዲፕሎማቶችን በመመደብ ልዩ ልዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዘርፉ ጥሩ ሥራ እየተሠራ መኾኑ በምክር ቤት አባላት ተነስቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሀገሪቱ በዘርፉ ከምትፈልገው ፈጣን ለውጥ፣ ከሚመደበው የሰው ኀይልና በጀት አንጻር ዲፒሎማቶች በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸው ስለመሆኑ፣ ለሀገሪቱ ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ኢንቨስትመንትና የውጪ ምንዛሬ አማራጮችን ከማቅረብ አንጻር፣ የሀገሪቱንና የሕዝቦቿን ፍላጎትና አቋም ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከማስገንዘብና በተለያዩ የሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር ውጤታማነታቸው ምን እንደሚመስል የማብራሪያ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰጡት ማብራሪያ ዲፕሎማሲውን ከተለዋዋጭ ሁኔታና ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ አንጻር ቃኝቶ መፈተሸና ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ካላት የምጣኔ ሀብታዊ አቅም አኳያ ብዛት ያለው የቆንስላ ጽሕፈት ቤትና ኤምባሲ እንደማያስፈልጋም ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ቁጥራቸውን ቀንሶ ዲፕሎማቶች በሀገር ውስጥ ሆነው እንዲከታተሉና በቀጠሮ እንዲያስፈጽሙ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
በቀጣዩ መስከረም በአዲስ የሚዋቀረው መንግሥት ይህን ሊያደርግ እንደሚችልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡
በሌላ በኩል አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ሳይከፈላቸው ከአምባሳደሮች የላቀ ሥራ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ጠቅሰዋል፤ እነዚህ አካላት ዲያስፖራውን እንዲያስተባብሩ ማድረግ ይጠበቃልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ዘርፉን ለማሻሻል የተጀማመሩ ሥራዎች መኖራቸውን በማንሳትም በቅርቡ አዳዲስ ወጣቶች በዘርፉ ሰልጥነው ተቋሙን የተቀላቀሉ ሲኾን በሂደት እንደሚጠናከር አመላክተዋል፡፡ እውነተኛ ወዳጅ ሀገራትም ለራስ ጥቅም ብቻም ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በአሸባሪው ሕወሓት ላይ የተወሰደው ርምጃ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን ለመከፋፈል የተሠራው ሥራ እንዲቀንስ ውጤት አምጥቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይቻልም፤ ለብዙ ኃይሎች ይህን ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ