“በአሸባሪው ሕወሓት ላይ የተወሰደው ርምጃ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን ለመከፋፈል የተሠራው ሥራ እንዲቀንስ ውጤት አምጥቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

118
“በአሸባሪው ሕወሓት ላይ የተወሰደው ርምጃ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን ለመከፋፈል የተሠራው ሥራ እንዲቀንስ ውጤት አምጥቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 27/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንዳሉት በሕግ ማስከበር ዘመቻው ጊዜ፣ ሀብትና ሕይወት ገብረናል፡፡ በተደከመው ልክ ለ40 ዓመታት የተዘራውን የዘረኝት መርዝ ማጥፋት አልቻልንም ነው ያሉት፡፡ የዘረኝት መርዙን ለማጥፋት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
ዘረኝነት ካንሰር መሆኑን ትምህርት ተገኝቶበት ካልሆነ በስተቀር ዘረኝነቱ መጥፋት አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተሠራው ክህደት “በአጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” የሚባለው አይነት ነበር ብለዋል፡፡
በነበረው ሕግ የማስከበር እርምጃ የአሸባሪው ኃይል አባል ሲገድል ጀግና ወታደራቸው ሲሞት ግን ንጹሕ ዜጋ ተደርጎ የሚቀርብበትን አውድ አይተናል ብለዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ተደጋጋሚ ትንኮሳ በማድረግ ያልተፈለገ አጸፋ እንዲፈጽም ሲገፋ ነበርም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በግዳጅ ወቅት የሚፈጠሩትን ጥቃቅን ስህተቶች ተጋነው እንዲስተጋባ ይደረግ ነበር ያሉት ዶክተር ዐቢይ ግጭቱ እንዳይቆም የሚፈልጉ ኃይሎች ከጀርባ ነበሩ ብለዋል፡፡ ዓላቸውም እንዳለፈው ሦስት አስርት ዓመታት ታሪካችን የደቀቀች ሀገር እንድትፈጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የውጭ ኃይሎችን ግፊት በሚመለከት ሲናገሩ ትግራይ አካባቢ ስለተፈጠረው ችግር የሚያወሩ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ ተጨንቀው ነው ብለን እንዳናስብ በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ስለተፈጠሩ ችግሮች ተስቷቸው እንኳን ሲያነሱ አላስተዋልንም ነበር ነው ያሉት፡፡
ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ ማየታቸውንም ገልጸዋል፡፡ የጥሞና ጊዜው መንግሥትን፣ ሕዝብንና እውነታውን ማወቅ ለሚፈልጉ ሀገራት እድል ይሰጣልም ብለዋል፡፡
ግጭቱን ማስቀጠል ስላልተቻለ ነው የወጡ የሚሉ ሰዎች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዓመታት ግጭት ማካሄድ የሚያስችል ልምምድ ነበር ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥነት መልማት እንጂ በፍጥነት ወደጦርነት መግባት አዲስ እንዳልነበር በመጠቆም፡፡ “ግጭቱን ማስቀጠል ውጤቱ መግደል፣ ረሃብ እና ዶላር መተኮስ ነው” ብለዋል፡፡
መስዋዕትነት ያስከፈለ ቢሆንም ሕግ የማስከበር እርምጃው ኢትዮጵያዊያንን እና ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የተደረገውን ጥረት ለመቀነስ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ “ለታመመች ዶሮ በሬ አይታረድም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በርካታ የልማት ክፍተቶች እያሉባት አላስፈላጊ ችግር ውስጥ መቆየቷ ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየ2014 የሀገሪቱ በጀት 561 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ኾኖ ጸደቀ፡፡
Next articleየኢምባሲዎችን እና የዲፕሎማቶችን ቁጥር መቀነስ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡