
“ኢትዮጵያ ላይ ግልጽ አደጋ እስካልመጣ ድረስ ከማንም ጋር ውጊያ አንፈልግም፤ በሰላም፣ በትብብር መልማትና ማደግ እንፈልጋለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግር እያደረጉ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ ላይ ግልጽ አደጋ እስካልመጣ ድረስ ከማንም ጋር ውጊያ አንፈልግም፤ በሰላም፣ በትብብር መልማትና ማደግ እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡
ሰላም እናስቀድማለን ለሰላም የሚከፈልን ማንኛውንም ክፍያ እንከፍላለን፣ ሰላም መፈለጋችን ክብራችን፣ ሰላም መፈለጋችን ህልውናችንን የሚነካ ከሆነ ግን ተገደን ሰላምን ለማምጣት የምንገባባቸው ግጭቶች ይኖራሉ ነው ያሉት፡፡
አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ አራት ግልጽ አደጋ ደቅኖ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰልጣን ላይ ከነበረበት ዘመን በተለዬ መንገድ ከመከላከያ የሚስተካከል ተቋም ለመግንባት የፌዴራል መንግሥት የሚሰጠውን በጀትና ቀድሞ ያዘጋጀውን ሀብት ወታደር ለማዘጋጀት ሠፊ ሥራ ሠርቷል፤ ወታደር እያዘጋጁ ሌላውን ካልነኩ ተዋቸው ብንል እንኳን ወታደር እያዘጋጁ በሌላው አካባቢ ችግር ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡
በአሸባሪው ሕወሓት በኩል ሁለተኛው ግልጽ አደጋ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅጠረኝነትና የቅጠረኞች ማስፋት አደጋ ነው፤ ሕዝብ ተረጋግቶ ወደ ልማት እንዳይገባ የሚያደርጉ ቅጥረኞች አሉ፣ የራሳቸውን ኃይል ከማደራጄት ባለፈ ገንዘብ እየሰጡ ሰላም እንዳይኖር በእቅድ የሚመራ አለ ነው ያሉት፡፡
ራሳቸው አፈናቅለው ዜና እንደሚናገሩም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወሱት፡፡ እያፈናቀሉ እኛ ብቻ ነን ሰላም ሲሉ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ቅጥረኞችን እንደ ወታደር ሲያዝዙ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ሦስተኛ አደጋ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ሕዝብ በድህነት ውስጥ ኾኖ ሳለ ከድኅነት ማውጣት ሲገባ ለጦርነት መቀስቀሳቸው ነው፡፡ በግራና በቀኝ ጦርነት ይነሳብሃል በማለት ሰፊ ሥራ ሠርተዋልም ብለዋል፡፡ ይህ ኹሉ ኾኖ በአሸባሪው የከፋው ጥፋት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጽም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሰሜን እዝ ለትግራይ ሕዝብ ጋሻ መከታ ሆኖ የጠበቀው መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብዙዎች የተገበሩበት፣ ሠራዊቱ ለሠራው ውለታ እንኳን ሲባል ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት መፈጸም አልነበረባቸውም ነው ያሉት፡፡ መከላከያውን ለማዋረድ የተሄደበት ርቀት አስደንጋጭ መሆኑንም ነው ያስታወሱት፡፡
አሸባሪው ሕወሓት የደቀነው አራተኛ አደጋ የፌደራል መንግሥት ሳይፈልግ በግድ ሀገሩን እንዲከላከል፣ የተቀማውን የሀገር ሀብት ለማስመልስ ወደ ግጭት ገብቷል ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ብዙ ጊዜ መለመኑንም አስታውሰዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በልመናው ጊዜ የነበራቸውን እብሪትም አስታውሰዋል፡፡
በሕግ ማስከበሩ ዘመቻው ጥፋተኛውን ብቻ ለይቶ የመምታት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡ ውጊያው በከተሞች ውስጥ እንዳይገባ የተደረገው ሙከራ የመከላከያ ሠራዊት ከፍ ወደ አለ ልእልና የሚወስደው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ጥፋተኛ የተባለን ኃይል ከመከላከያ ሠራዊትም ተጠያቂ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ጥፋተኛ የተባሉ የሕወሓት ሰዎችም ዘመናዊ በሆነ መንገድ እንደተያዙ ነው የገለጹት፡፡ ሲገርፉ ነበርና እንግረፋችሁ አላልነምም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ትግራይ ክልል ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንዳይነካ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡ ግብርና፣ ትምህርትና ጤና ሥራ እንዲጀምር ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የነበረውን ቀውስ ለማረገብ 100 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በተደረገው ውጤት ያጠፉትን መያዝ ተችሏል፣ ሰሜን እዝ ነጻ ወጥቷል፣ ትጥቅ ነጻ ወጥቷልም ነው ያሉት፡፡ ከኹሉም በላይ መከላከያ ሀገራዊ ሆኖ እንዲገነባ መልካም እድል ተገኝቷልም ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ