
‹‹ክብራችን ለማስመለስ አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡ በምክር ቤት አባላትም ወቅታዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ በሀገሪቱ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት አንዱ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዋጋ ግሽበት መንስኤ ያሏቸውን ነጥቦች ለምክር ቤት አባላቱ አብራርተዋል፡፡
የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም፣ ምርትም እያለ የንግድ ሰንሰለት ችግር መኖር፣ ወደ ገበያ የሚለቀቀውን ገንዘብ የመቆጣጠር ችግር፣ በዓለም ላይ ያለው የዋጋ ጭማሪ፣ አምራቾች ምርትን መያዝ እና ሸማቾችም ምርትን ገዝቶ ማከማቸት ለዋጋ ግሽበቱ መንስኤዎች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል፡፡
ችግሩንም ለመፍታት መንግሥት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ምግብነክ ምርቶች እንዲገቡ ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕብረት ሥራ ማኅበራትም ተጨማሪ በጀት በመመደብ ሸቀጦች እንዲከፋፈሉ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ የግሉ ሴክተር መሠረታዊ ሸቀጦችን እንዲያስገቡ መደረጉንም አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የገንዘብ እና የፊሲካል ፖሊሲ ቁጥጥር ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡ የንግድ ሥርዓቱን የማስተካከል ሥራ እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡
ምርት ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሠጥቶ እንደሚሠራም አስቀምጠዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አንድም የመንግሥትም ሆነ የግል መሬት ጦም ማደር እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡
“ስንዴ የሚለምን ሕዝብ እና ሀገር ክብር የለውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ክብራችን ለማስመለስ አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም” ነው ያሉት፡፡ የበጋ ስንዴ ምርት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡
የተበጣጠሰ መሬትም ቢሆን በኩታ ገጠም የሚመሳሰል ምርትን የማልማት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ መንግሥትም የቴክኖሎጅ ውጤቶችን እና የብድር አቅርቦትን የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
መሠረታዊ ሸቀጦች ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ እንደሚሠራ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የግብይት ሥርዓት ለማስፋት ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ