
የስድስት ከተሞች የመረጃ አስተዳደር (ፖርታል) በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 27/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የከተሞች መረጃ አስተዳደር (ፖርታል) ከተሞች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የሚሠሩትን ሥራ ሕዝብ እንዲያውቅላቸው፣ የሚሰጡት አገልግሎት እንዲተዋወቅ፣ ከውጭ የሚመጡ ሰዎች የተሟላ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ነው።
አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ ሃዋሳ፣ አዳማ እና አርባምንጭ ከተሞች የከተማ መረጃ አስተዳደር (ፖርታል) እየለማላቸው ሲሆን ራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ ለባለሙያዎቻቸው በሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት የግንዛቤ ማስጨባጫ እየተሰጠ ይገኛል።
ከተሞቹ የመረጃ አስተዳደሩን እንዲያስተዳድሩ፣ መረጃ እንዲያከማቹ፣ አዳዲስ ማሻሻያዎችን እንዲጨምሩ፣ አጠቃቀሙን እንዲያውቁ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።
የከተማ የመረጃ አስተዳደር (ፖርታል) የከተማ ነዋሪዎችና ከከተማ ውጭ የሚኖሩ ሰዎች ስለ ከተሞች የሚፈልጉትን መረጃ ባሉበት ሆነው እንዲያገኙና የከተማዎቹ ነዋሪዎች መንግሥት የሚሰጠውን አገልግሎት ባሉበት ሆነው እንዲያገኙም ያስችላል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ባዩ (ዶ.ር) የከተማ መረጃ አስተዳደር ዜጎች በቂ መረጃ እንዲያገኙና ከተሞች እድገታቸው እንዲፋጠን ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በቀጣይ ሌሎች ከተሞችም የከተማ የመረጃ አስተዳደር (ፖርታል) እንዲኖራቸው እንደሚሠራም አብራርተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየሁለት ዓመቱ የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ የሚወጣ ሲሆን ይህ ሥራም ኢትዮጵያ ያላትን ደረጃ ለማሻሻል የሚሠሩ ሥራዎች አካል መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ