“ኢትዮጵያ ዓባይን አልምታ ምጣኔ ሀብቷን ማሳደግ እና ዜጎቿን መመገብ ነው ዓላማዋ”ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

87
“ኢትዮጵያ ዓባይን አልምታ ምጣኔ ሀብቷን ማሳደግ እና ዜጎቿን መመገብ ነው ዓላማዋ”ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት 4ኛ ልዩ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡ በምክር ቤቱ ስብሰባ አባላቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌትን አስመልክቶ ላነሱት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ዓባይን አልምታ ምጣኔ ሀብቷን ማሳደግ እና ዜጎቿን መመገብ ነው ዓላማዋ ብለዋል፡፡ ቀሪው ዓለም የኢትዮጵያን እውነት በመገንዘብ ጉዳዩን በሰላም ለመቋጨት ሊያግዝ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ መብራት ከመስጠት ባለፈ ለግብጽ እና ሱዳን የጎርፍ አደጋ ይቀንሳል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሂደቱን ለማጓተት ከሚታትሩት ጉልበት ቀንሰው በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመሳተፍ የውኃ መጠኑን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
በመንግሥት ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን ስርቆት እና ሙስና እንዴት ማስቆም አስባችኋል? በሚል ለተነሳው ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ችግሩ የመንግሥትን መዋቅር በእጅጉ እየፈተነ ያለ ድርጊት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ “ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጊዜ እና ሀሳብም እየተሰረቀ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቀጣይ የትኛውም ፓርቲ አሸንፎ መንግሥት ይመስርት ሌብነትን በማስወገድ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ እርምጃዎች መኖራቸውን ጠቁመው መስፋት ይጠበቅባቸዋል፤ ሕዝቡም ለዚህ ድጋፍ መስጠት አለበት ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ ሌባ ለየትኛውም ብሔር ሆነ ሃይማኖት እንደማይጠቅም በማመን ለመንግሥት መረጃ በማድረስ እና ለሚወሰደው እርምጃ ተባባሪ በመሆን እንዲያግዝም ጠይቀዋል፡፡
በተለይም በከተሞች አካባቢ ጥቃቅን ጉዳዮችን ለማስፈጸም ሕዝቡ ከፍሎ አገልግሎት የሚያገኝበት መንገድ መታረም እንደሚኖርበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየውጪ ኢንቨስትመንትን 20 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
Next articleየስድስት ከተሞች የመረጃ አስተዳደር (ፖርታል) በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡