
“የኢትዮጵያ የውጭ እዳ ጫና በጠቅላላ ዓመታዊ እድገት አንፃር ሲታይ ከነበረበት 37 በመቶ ወደ 26 በመቶ ገደማ ወርዷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት 4ኛ ልዩ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡ ምክር ቤቱ እያካሄደው ያለው ልዩ ስብሰባ የ2014 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላቱ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነሱት ጥያቄዎች በሁለት ጎራ ለይተዋቸዋል፤ ምጣኔ ሃብታዊ እና ወቅታዊ በማለት፡፡
ያለፈው በጀት ዓመት በርካታ ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች ነበሩበት ያሉት ዶክተር ዐቢይ ኮሮናቫይረስ፣ አምበጣ፣ ጎርፍ፣ ግጭት፣ መፈናቀል፣ የዘገዩ ፕሮጀክቶች፣ ስደት እና ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴውን ፈትነውታል ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ የውጭ እዳ ጫና በጠቅላላ ዓመታዊ እድገት አንፃር ሲታይ ከነበረበት 37 በመቶ ወደ 26 በመቶ ገደማ ወርዷል ነው ያሉት፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት በገቢ እና በወጭ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እየተሠራ በመሆኑ አንፃራዊ ለውጦች ተመዝገበዋል ነው ያሉት፡፡
ያለፈው በጀት ዓመት ፋይናንሻል እንቅስቃሴ በተመለከተ 6 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን “500 የሚደርሱ ወረዳዎች አንድ የባንክ ቅርንጫፍ እንኳን የላቸውም” ነው ያሉት፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመለየት ፍትሐዊ የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲኖር ይደረጋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ