ʺ ምስጢር የሞላው መሶብ፣ ጥበብ ያለበት አምሳለ ልብ”

330
ʺ ምስጢር የሞላው መሶብ፣ ጥበብ ያለበት አምሳለ ልብ”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምድርን ፈጠራት፣ በፈጠራት ምድር ይኖሩ ዘንድ ፍጥረታትን ፈቀደላቸው። ከፈጠራት ምድር ሁሉ የላቀች ምድር አለች። የምድር ገዢ ሁሉ እንዲቀመጥባት የተፈቀደላት። ከኤዶም ገነት የሚፈሰው ውኃ ይከባታል። ያጠጣታልም። ዘመናት አለፉ፤ የሰው ልጅ በደለ። የጌታ የፈጣሪ ዓይን ምድርን ተመለከታት። በቁጣም ቀጣት። ምድርን ንፍር ውኃ አጥለቀለቃት፡፡ በምድር የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ ስለ በደል ጠፉ፡፡ ነገር ግን ዘር ቀርቶ ነበር፡፡ ምድርን ያለ አንድ ሰው አልተዋትም እንዳለ ከበደለኞች መካከል በደል ያልተገኘበት፣ ጥፋት ያልተመዘገበበት፣ መንገዱ ሁሉ በእውነተኛው የሆነ አንድ ሰው ነበር። ይህም ሰው ኖህ ይባላል። ኖህም በዚያች ቅድስት ምድር ይኖር ነበር ይባለል። ያቺም ቅድስት ምድር ኢትዮጵያ ናት ይላሉ አበው።
የጥፋት ዘመን የታለፈበት፣ የኖህ መርከብ የተንሳፈፈበት፣ ምድር የረጋበት፣ ሌላ ዘመን የተጀመረበት፣ መርከቡም ያረፈበት ሚስጥራዊ ሐይቅ። በውኃ ክምችት የሚበልጡት ሐይቆችና ውቅያኖሶች ቢኖሩም በምስጡር ግን አንዳቸውም አይደርሱበትም፡፡ እርሱ ከውኃም በላይ ጥበብ፣ ታሪክ፣ እሴት፣ ተስፋ ነውና- ጣና ሐይቅ፡፡ ጣና ከሐይቁ ጥልቀት የሚስጥሩ ጥልቀት ይልቃል ይላሉ አበው። ለምን ካሉ ገደማት፣ አድባራት፣ ምስጢራት፣ በረከት፣ መንፈስ ቅዱስ ይዟልና ነው። በጣና ላይ አቡነ ሂሩት አምላክና አባ ማንእንደአባ በድንጋይ ታንኳ አልፈዋል። በፅናት ባመጡት ቅድስና ሐይቁንም ቀድሰውታል። በዚህ ሐይቅ አባ አትማረኝም የተባሉ አባትም ያለ ታንኳ በእግራቸው ተራማምደውበታል ይላሉ አበው። አሁንም ዝጉሃን አባቶች በጣና ውስጥ በቅዱስ መንፈስ ይመላለሳሉ። ዓለማውያን መንፈሳዊያንን አያውቁም። መንፈሳዊያንም ዓለማውያንን አያውቋቸውም። ዓለም እነዚያን አባቶች አታውቃቸውም። አባቶችም ከንቱዋን ዓለም አያውቋትም። አይፈልጓትም። ይንቋታል እንጂ። ጤዛ እየላሱ፣ ድንጋይ እየተንተራሱ፣ ድምፀ አራዊቱን ፀበዓ አጋንቱን እየታገሱ፣ ይፆማሉ ይፀልያሉ። ፀሎታቸውም ለእነርሱ ብቻ አይደለም። ለኢትዮጵያ፣ ለሕዝቦቿ፣ ለዓለም ነው እንጂ። እኒያ አባቶች የዓለምን ግብር ይንቋታል እንጂ ስለ ዓለም ግን ሳያቋርጡ ይፀልያሉ። ትጠፋ ዘንድ አይፈልጉም፣ ለዓለም ያዝኑላታል፡፡ ዓለም ፈጣሪዋን ትተዋለችና ፈጣሪም ዓለምን እንዳይተዋት። የቁጣው በትሮች እንዳይወረወሩ የመሰሉት አብዝተው ይለምናሉ።
ጀንበር በምሥራቅ ንፍቅ እየተፍለቀለቀች ነው፡፡ የሰርግ ጊዜዋ የደረሰች ሙሽራ ትመስላለች፡፡ ፍልቅልቅ፣ ውብ ገጽታ ያላት፡፡ መነሻቸውን ከባሕርዳር የሚያደርጉ ጀልባዎች በጠዋት ሽርጉድ ላይ ናቸው፡፡ በማዕበል ሲናጥ ያደረው ጣና እየተረጋጋ ነው፡፡ ጀልባ ፈላጊ…. ጀልባ ነው….. የሚሉ ድምጾች በርክተዋል፡፡ ወደ ሐይቁ ዳርቻ እያዘገምኩ ነው፡፡ በቀኝና በግራ ትንንሽ ጀልባዎችን አሰልፋ የቆመችው ግዙፉ ጀልባ ለጉዞ ተዘጋጅታለች፡፡ ከግዙፉ ጀልባ ፊት ለፊት ወደ ውስጥ የሚዘልቁትን ሰዎች የጉዞ ማረጋገጫ ወረቀት የሚቀበሉ ሰዎች ቆመዋል፡፡ እጓዝ ዘንድ ማረጋገጫ የምትሆነኝን ወረቀት ከኪሴ አውጥቼ እጄን ዘረጋሁ፡፡ ወደ ግዙፏ ጀልባ እንድገባ ፈቃድ ተሰጠኝ፡፡ አመሰግኜ ወደ ውስጥ ዘለኩ፡፡ በውስጡ የተቀመጡት ሰዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያወጉ አይሰማም፡፡ አብዝኛዎቹ ዝምታን መርጠዋል፡፡ ጥቂቶቹ ብቻ በለሁሳሳ ይነጋገራሉ፡፡ ቦታ መርጨ ጉልበቴን አሳረፍኩ፡፡ ለጉዞ የተዘጋጄችው ጀልባ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡
ጣና የገዳማትና የአድባራት፣ የቅዱስ መንፈስ፣ የምስጢራት፣ የጠቢባን፣ የሊቃውንት፣ የመነኮሳት፣ የቀሳውስት መገኛ የጋራ ቤት፡፡ የምድርን የቀደመ ታሪክ፣ ስልጣኔ፣ ጥበብና ሃይማኖትን ለመማር የሚሹ ሁሉ ባሕራትን እየተሻገሩ፣ ምድርን እያቆራረጡ ወደ ኢትዮጵያ ይተማሉ፡፡ ኢትዮጵያ የጥበብ፣ የምስጢር፣ የታሪክ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የፍልስፍና የሁሉም መገኛ መሶበ ወርቅ ናትና፡፡ ኢትዮጵያን የተከተለ እንጂ የቀደመ የለም፡፡ ዓለም እንደ ኢትዮጵያ የምትፈልጋት ሀገር ያለች አትመስልም፡፡ ፍላጎቷ በመልካምም በክፉም ሊሆን ይችላል እንጂ፡፡
ጀልባዋ መልሕቋን ሰብስባ ጉዞ ጀምራለች፡፡ ሐይቁን እየከፈለች በዝግታ ስትጓዝ ደስታን ይሰጣል፡፡ በጀልባዋ ውስጥ የነበሩ ተጓዞች ነጫጭ ልብሶችን ለብሰዋል፡፡ ዓይኔ አድማስ እስኪመልሰው ድረስ በትዝብት ይመለከታል፡፡ በጀልባዋ ውስጥ የነበረው ዝምታ ተሰብሮ ዝማሬ ተጀምሯል፡፡ ʺሰላም ለኢትዮጵያ ሰላም ለሀገራችን፣ ይልካልን ቸሩ አምላካችን” ይላሉ በጋራ፡፡ አዎን ምድር በንፍር ውኃ ስትጠፋ ፍጥረት እንዲተርፍባት የተመረጠች፡፡ የመከራውን ዘመን ያሳለፈችው መርከብ እንድታርፍባት የታደለች፣ ለምስክርና ለክብር ትሆን ዘንድ የተጠበቀች፣ ዓለምን መርታ ያሻገረች፣ በጨለመ ዓለም ውስጥ ከተራራ ላይ እንደተሰቀለ ብርሃን በአሻገር የታዬች ድንቅ ሀገር ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ዝማሬው ደምቋል፡፡ ዓይኔ በእርጋታ የተኛውን ሐይቅ እየተመለከተ፣ ጆሮዬ የኅብረት ዝማሬ እየሰማ፣ እዝነ ልቦናዬ ስለ ሐይቁ እያንሰላሰ ጉዟችን ቀጥሏል፡፡
እንጦስ ኢየሱስና ክብራን ገብርኤል ገዳማትን በስተ ግራ በኩል በቅርብ ርቀት ተመልክተናቸው አለፍን፡፡ የረጋው ጣና ውበቱ ልዩ ሆኗል፡፡ በሐይቁ ውስጥ በጥበብ በተቀመጡ ደሴቶች፣ በደሴቶቹ በሚኖሩ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ውጪ ለዓለማውያን የተሰወሩ፣ ለዝጉሃን እና ለሥውራን አባቶች የተገለጡ ረቂቅ ቦታዎች ይኖሩ ይሆን ስል አሰብኩ፡፡ ጣና ከሚያዩት የላቀ፣ ከሚታሰበው በላይ የረቀቀ፣ ከምንም የጠለቀና የመጠቀ ነውና፡፡ ቅዱስ መንፈስ የሚጠብቃቸው፣ ቅዱሳን አባቶች የሚመላለሱባቸው፣ በቅድስና የሚኖሩባቸው ያልታዩ ቦታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እያንሰላሰልኩ ጀልባዋ ሐይቁን በእርጋታ እየከፈለች ወደ ፊት ገሰገስን፡፡ በአሻገር አምሳለ የኖህ መርክብ እየተባለ የሚጠራው ዳጋ እስጢፋኖስ ደሴት ይታያል፡፡ ዳጋ እስጢፋኖስ የምስጢር ቦታ፤ ወደ ምሥራቅ ንፍቅ ትተነው ወደ ፊት ጉዞአችን ቀጠልን፡፡
ʺለዓለማት ሁሉ ኢትዮጵያ ተስፋነሽ
አይደለሽም ብዙ በቁጥር አንድ ነሽ” የጋራ ዝማሬው ቀጥሏል፡፡ አዎን የዓለማት ሁሉ ተስፋ የሆነች ሀገር ናት፡፡ ከዓለት የጠነከረች፣ በመከራ ዘመን የጸናች፣ በወጀብ ያልተናወጠች፣ በጥል ያልወደቀች፣ በጦርነት ያልተሸነፈች፣ በፍቅር ያቀፈች፣ በጥበብ ያራመደች አንዲት ጽኑ ሀገር ናት -ኢትዮጵያ፡፡
ʺዥንጉርርነቱን ነብር አይቀይርም
ኢትዮጵያዊ መልኩን ሊለውጥ አይችልም” ልብን እያረሰረሰ መንፈስን የሚያድሰው ዝማሬ ልቤን ቀስሮ ይዟታል፡፡ ሰዓታት ተቆጥረዋል፡፡ ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ አዎን ኢትዮጵያዊ መልኩን ሊለውጥ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ምስጢር፣ ኢትዮጵያዊነት ክብር፣ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነውና፡፡ መዳረሻችን ደሴት በአሻገር እየታዬ ነው፡፡ የሰማይ አሞራዎች ክንፍና ክንፋቸውን ገጥመው በጣና ሐይቅ ሰማይ ሥር እንዳሻቸው ይሆናሉ፡፡ ከፍ ዝቅ እያሉ ወዲያና ወዲህ ሲመላለሱ ደስታ ይሰጣሉ፡፡ ዓይኔ መልካም ነገር እያዬ ነው፣ ጆሬዬም መልካም ነገር እየሰማ ነው፣ ልቤም መልካም ነገር እያሰበ ነው፣ ነብሴ ተደስታለች፣ አቤቱ የሰው ልጅ ሁሉ በሚቀናባት ምድር ፈጠርከኝ፣ ጠብቀህ አሳደከኝ፣ ፈቅደህ መልካም ነገር እንዳይ አደረከኝ፣ ስንቶች ይሆኑ ይሆኑ ያን ሥፍራ ለማዬት ጓጉተው ሳይሳካላቸው የቀረው እኔ ግን ሁሉን አግኝቻለሁና ተመስገን አልኩ በልቤ፡፡
ድንቋ ምድር ኢትዮጵያ ሆይ መታደልሽ፣ ቅዱሳን ይኖሩብሻል፣ የሰማይ መላእክት ይጠብቁሻል፣ ልጆችሽ ይኮሩብሻል፣ ኮርተውም ያኮሩሻል፣ ፍጥረታት ያደንቁሻል፣ ያዩሽ ዘንድ ይመኙሻል፣ ሳያውቁሽ ዝናሽን ሰምተው ይናፍቁሻል፣ በናፍቆትሽ ይጎዳሉ፣ በፍቅርሽ ይደማሉ፣ እንቺን እያሰቡ በቤትሽ ይጠለሉ ዘንድ ይተማሉ፣ ማነው እንደ አንቺ የተፈለገ ? ተመርጠሻልና እንዳንቺ ያለ የለም፡፡
ʺበታላቁ መዝገብ ስምሽ የሰፈረ
የቆዬው ድንበርሽ እንደተከበረ
ያኑርሽ ፈጣሪ አንቺን ከፍ አድርጎ
መሃልሽን ገነት ዳሩን እሳት አርጎ ” የዚያ ውብ ዝማሬ ግጥሞች ኃይላቸው ብርቱ ነው፡፡ እልፍ ነገሮችን በውስጣቸው ይዘዋል፡፡ ከመዳረሻችን ወደብ ደርሰናል፡፡ ጀልባዋ መልሕቋን ዘረጋች፡፡ ከፊት ለፊታችን የሚገኘው በአረንጓዴ ካባ የተሸበበው ገዳም አስፈሪ ግርማውን ተላብሶ ይታያል፡፡ ጀልባዋ ከቆመችበት ትንሽዬ ወደብ አጠገብ የጎንደር አብያተ መንግሥታትና አብያተ ክርስቲያናት በተሠሩበት ጥበብ የተሠራ የገዳሙ መግቢያ በር አለ፡፡ በትንሿ ወደብ አልፈው ወደ ውስጥ የሚዘልቁትን ተጓዦች ተከትዬ ወደ ውስጥ ዘለኩ፡፡ በእንቁላል ግንቡ ሥር በተሠራችው በር አልፈን ወደ ውስጥ ተጠጋን፡፡
አጸደ ግቢው ውብ ገጽታ ተጎናጽፏል፡፡ የቤተክርስቲያኑ ዙሪያ ገባ በጥበብ በተሠራ ካብ ታጥሯል፡፡ በረጃጅም ዛፎች አናት ላይ የተሰቀሉ አዕዋፋት ይዘምራሉ፡፡ በነፋስ በቀስታ የሚወዛወዙት በቤተክርስቲያኑ አጸድ ዙሪያ የቆሙት ዛፎች፣ ለፈጣሪያቸው ምስጋና ለምዕምናን ደግሞ አቀባበል የሚያደርጉ ይመስላል፡፡ ውብ ሥፍራ ድንቅ ጥበብ፡፡
ገዳመ ናርጋ ሥካሴ አጸድ ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ ታላቋ ንግሥት እቴጌ ምንትዋብ በጎንደር አብያተ ምንግሥታት ውስጥ በክብር ናቸው፡፡ ልጃቸው ኢያሱ ደግሞ ዙፋኑን ይዘውታል፡፡ የመናገሻዋ ከተማ ጎንደር ስሟ ኃይል ሆኗል፡፡ በዚህም ዘመን የውጭ ጠላት ድንበር ዘሎ ሊገባ ያሰፈስፍ ፈልጓል፡፡ በጎንደር አብያተ መንግሥታት ነጋሪት አጓራ፣ አዋጅ ተነገረ፣ ኢያሱ የሀገራቸውን ድንበር ሊያስብሩ ለዘመቻ ተዘጋጁ፡፡ ስንቅና ትጥቅ ተዘጋጀ፡፡ ወደ ዘመቻም ሄዱ፡፡ እናታቸው ገናናዋ እቴጌ ምንትዋብ ግን በቤተ መንግሥት ቀርተው ነበር፡፡ ንጉሡ ኢያሱ ለዘመቻ ሄደው ጠላት ሲመልሱ፣ ሀገር ሲያረጋጉ በዚያው ቆዩ፡፡ የልጃቸው ቶሎ አለመመለስ እቴጌዋን አስጨነቃቸው፡፡ የእናት ሆድ ተንሰፈሰፈ፡፡
ለፈጣሪያቸውም ስለት ገቡ፡፡ ʺ ልጄ ሀገሩን አስከብሮ ጠላቱንም አሳፍሮ በሰላም ተመልሶ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት ቢያበቃኝ የሥላሴን ቤተ መቅደስ አንጻለሁ” ሲሉ ስለት ተሳሉ፡፡ ስለታቸውን በልባቸው ይዘው አደራውንም ለጌታቸው ሰጥተው የልጃቸውን መምጣት እየተጠባበቁ ተቀመጡ፡፡ በዚያ ዘመን በታሪካዊቷ ጀበራ ማርያም ውስጥ የሚኖሩ አንድ የበቁ አባት ነበሩ፡፡ ስማቸው አባ እኖሪዮስ ይባሉ ነበር፡፡ በጣና ሐይቅ አሳ እያሰገረ የሚኖር አንድ አሳ አስጋሪም ነበር፡፡ እኒያ አባትም ወደ ዚያ አስጋሪ ሄዱ፡፡ ለአሳ አስጋሪውም መልእክት ነገሩት፡፡ ʺ ሂድና እቴጌ ምንትዋብን ልጅዎ በሰላም ይመጣል፣ የተሳሉትን ስለት እንዳይረሱ፣ የሚሰራውም በደሴት ውስጥ ነው፡፡ ይህን ሳያደርጉ ቢቀሩ ግን ወደፊት ብዙ ፈተና ያጋጥምወታል” ብለህ ንገራቸው አሉት፡፡
ያ አሳ አስጋሪም ʺ አባቴ ሆይ እኔን ከቤተ መንግሥት ማን ያስገባኛል” አላቸው፡፡ ልጄ ሆይ እንደነገርኩህ ሂድ አንዲት አሳ ለምልክት ይዘህ ሂድ፣ እኔም አልለይህም፣ ያዘዝኩህን ፈጽም” አሉት፡፡ አሳ አስጋሪው የተጣለበትን ታላቅ መልእክት ይዞ ወደ ቤተመንግሥት አቀና፡፡ ቤተ መንግሥትም ደረሰ፡፡ ለቤተ መንግሥት ጠባቂዎችም መልእክት ተልኬ ነው የመጣሁት አላቸው፡፡ መልእክቱስ ምንድን ነው አሉት፡፡ መልእክቱንስ ለእሳቸው ነው ንገር የተባልኩት ከእሳቸው ውጪ ለማንም አልነግርም አላቸው፡፡ አደራው ከባድ መልእክቱም ኃያል ነበርና፡፡ ለማንም አይነገርም፡፡ የቤተ መንግሥት ጠባቂዎችም ወደ ውስጥ ዘልቀውʺ እቴጌ ክብር ለእርሶ ይሁን፣ ከቤተ መንግሥት በር ላይ ለእርሶ መልእክት ይዤ መጣሁ የሚል አንድ ሰው አለ፤ መልእክቱ ምንድነው ንገርን ብንለው ለእርሳቸው ብቻ ነው የምናገረው አለን፣ ምን እናድርግ?” አሉ፡፡ እቴጌዋ መልእክተኛው ይገባ ዘንድ ፈቃድ ሰጡ፡፡ መልእክተኛውም ገባ፡፡ የተባለውን ሳያጓድል አደረሰ፡፡
እቴጌ የደረሳቸው መልእክት ኃያል መሆኑን ያውቁ ነበርና፣ ሊቃውንትንና መኳንንቶችን አስከትለው የደንገል ታንኳ አሠርተው፣ ስሩበት ወደተባለው ሥፍራ አቀኑ፡፡ መልእክቱን ያለኩት አባትም አገኟቸው፡፡ የሚሰሩበት ሥፍራ ያ ደሴት ነው፣ ስለትዎን ይፈጽሙ፣ ልጅዎንም ሲመለሱ ያገኙታል አሏቸው ፡፡ እቴጌዋ ሥፍራውን ዓይተው ወደ ቤተ መንግሥት ተመለሱ፡፡ በተመለሱም ጊዜ አጼ ኢያሱ ጠላትን አሸንፈው፣ ድንበራቸውን አስከብረው ተመልሰው ተገናኙ፡፡ በቤተ መንግሥት ደስታ ሆነ፡፡ ግብር ተበላ፡፡ ዜማ ተዜመ፣ ምስጋናም ቀረበ፡፡ ከዚያም እቴጌዋ በልባቸው የያዙትን ለልጃቸው ነገሯቸው፡፡ ወደ ደሴቱም በደንገል ታንኳ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ይሰራበት ዘንድ የታዘዘውን ደሴት ዞሩት፡፡ ወደ ደሴቱም ገቡ፡፡ በደሴቱ ውስጥም ታላቅ የዋርካ ዛፍ ነበር፡፡ እቴጌዋም ከዋርካው ግርጌ ተቀምጠው ጸሎት ማድረስ ጀመሩ፡፡ እንቅልፍም ወሰዳቸው፡፡ ራዕይ ታያቸው፡፡
የታያቸውን ራዕይ አብረዋቸው ለተጓዙት ሊቃውንት ነገሯቸው፡፡ ሊቃውንቱም ራዕዩን ፈቱ፡፡ በዚህም ʺእንርጋ” አሉ፡፡ በዚያም ቤተ መቅደሱ ታነጸ፡፡ ውብ ቤተ መቅደስ፣ ጥበብ ያረፈበት፣ ለቤተ መቅደሱ መሥሪያ የሆነውም እቴገዋ ከቤተ መንግሥት መጥተው ያረፉበትና ራዕይ ያዩበት ዋርካ ነው፡፡ ሥራው ሲጠናቀቅም ገዳመ ናርጋ ሥላሴ ብለው ሰየሙት፡፡ በዚያውም ጸና ነው ያሉኝ የገዳሙ አስተዳዳሪ ቄስ ታለማ ቸኮል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ 29 ቆመ ብሴዎች አሉት፤ በዙሪያውም ሰባት ግንቦች አሉት፡፡ አስራ ሁለት በሮች፣ ሃያ አራት መስኮቶችም አሉት፡፡ በሮችም በጥበብ የታነጹ፣ ውብ የሆኑ ናቸው፡፡ ልቤ እየራደች ወደ ውስጥ ዘለኩ፡፡ አብዝቶ ገረመኝ፡፡ አቤቱ ምን አይነት ጥበብ አረፈበት፣ ምን አይነት እጆች ተጠበቡበት፣ ምን አይነት ቅዱስ መንፈስስ አደረበት፤ ዋለበት አልኩ፡፡ በዙሪያ ገባው የተሳሉት ጥንታዊ ሰላድኖዎች ከመገረም በቀር ምን ይባላሉ፡፡ እጹብ ብሎ ማለፍ ይሻላል እንጂ፡፡ ዙሪያውን ተመለከትኩ አጄብ ያሰኛል፡፡ በዚያው ውስጥ ያለ ምክንያትና ያለ ምልክት የተቀመጠ፣ የተደረገ ነገር የለም፡፡
በዚያ ገዳም ውስጥ እቴጌዋ ሀገራቸው ሰላም እንድትሆን፣ ዙፋን እንዲጸና፣ ሀገር እንዲቀና፣ በረከት በምድር እንዳይርቅ ሱባኤ ይገቡበት እንደነበር ይነገራል፡፡ በታላቁ ገዳም ውስጥ አጼ ኢያሱ ሀገሩን አስከብሮ የተመለሰበት ጎራዴ ይገኛል። ጎራዴውም ከብር የተሠራ ነው ብለውኛል አበው፡፡ ሰገባው ደግሞ በቆዳና በወርቅ የተሠራ ነው። ኤቴጌ መንትዋብ ፈጣሪያቸውን ሲማጸኑ የሚያሳይ በሕብረ ቀለማት የተዋበ ስእልና አያሌ ጥበባት ይገኙበታል። በየወሩ በባዕለ ሥላሴ የሚወጣው ፈዋሴ ድውያን የተሰኘ መስቅልም በዚያ ገዳም ውስጥ አለ፡፡ የእምነቱ ተከታዮችም በወር አንድ ጊዜ ብቻ በሚወጣው መስቀል ለመፈወስ ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ሰምቻለሁ፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲመጣ ንጉሡ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መቅደሱን አስጠግነዋል፡፡ ቤተ መቅደሱ አሁንም ጥበቡን ሳያጣ መታደስ እንደሚገባው አስተዳዳሪው ነግረውኛል፡፡
የአዕዋፋት ዝማሬ፣ የዛፎቹ ሽብሸባ እንደቀጠለ ነው፡፡ ተዘዋውሬ ተመለከትኩት የሚጠገብ አይደለም፡፡ በዚያ ውስጥ በሚኖሩት ጀንበር ብርሃኗን በሰጠች ቁጥር በሚመለከቱት፣ ከታዛው በሚያርፉት ቀናሁ፡፡ ከውብ ነገር ርቄ እንደመኖር ተሰማኝ፤ የገዳመ ናርጋ ቆይታዬ ተጠናቀቀ፡፡ በተዋበው ደሴት ሥር ለሥር ተሹለክልኬ ወደ ወደቡ ወረድኩ፡፡
ጀልባዋ ለመንቀሳቀስ ተዘጋጅታለች፡፡ ገዳመ ናርጋን በስስት እየተመለከትኩት፣ ከአጠገቡ ርቀን ተጓዝን፡፡ መደመሜን ቀጥያሉ፡፡ ጀልባዋ ሐይቁን እየሰነጠቀች ግርማ ወደ ተላበሰው ሥፍራ አቀናች፡፡ በአሻገር የሚታዬው አረንጓዴ ሥራ በውስጡ ምንም አይነት ክፍተት ያለው አይመስልም፡፡ ውበቱ ከሩቅ ይጠራል፡፡ ጀልባችን እየቀረበች ነው፡፡ ዘጌ ደርሰናል፡፡ ውብ ስፍራ፣ ቅዱስ ምድር፣ ጀልባዋ መልሕቋን ዘርግታ ተመቻችታ ቆመች፡፡ በጀልባው የነበሩ ሁሉ እየወረዱ ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ ይሰገሰጉ ጀምረዋል፡፡ ተከትያቸው ገባሁ፡፡ የዥግራ መንገድ በምትመስለው ቀጭን መንገድ ወደ ላይ ወጣን፡፡ በየመንገዶቹ ጌጣጌጦችና ፍራፍሬ የሚሸጡ ሰዎችን እያገኘን ነው፡፡ ከመንገዷ ግራና ቀኝ በአሻገር ማዬት አይቻልም፡፡ መልካሙ ምድር በአረንጓዴ ተውቧልና፡፡
ወደ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እየገባን ነው፡፡ ዙሪያው በጥበብ በተሠሩ ድንጋዮች የታጠረ ነው፡፡ ቅጽሩ ውብ ነው፡፡ መልካም ማዕዛ አካባቢው ሲያዳርሰው ይታወቃል፡፡ ታላቁ አባት አቡነ በትረማርያም በመንፈስ ቅዱ መሪነት በዚያ ሥፍራ መጥተዋል፡፡ በዚያም ለፈጣሪያቸው ምስጋና እያቀረቡ ይኖሩ ነበር፡፡ በዘመኑ ንጉሥ አምደ ጽዮን ነግሠው ሀገር ያስተዳድሩ ነበር፡፡ አቡነ በትረማርያምም በተቀደሰው ሥፍራ የተቀደሰ ቤተ መቅደስ ያንፁ ዘንድ ፈቃድ እንዲሰጧቸው ንጉሡን ጠየቁ፡፡ ንጉሡም ፈቀዱ፡፡ ቤተ መቅደሱም ታነጸ፡፡ ድንቅ ቦታ፣ ቅዱስ ምድር፡፡ ዙሪያ ገባውን ተመለከቱክት ታይቶ አይጠገብም፡፡ ከአጠገቡ ወደሚገኘው አቡነ በትረማርያም ቤተክርስቲያን አቀናሁ፡፡ አጠገብ ለአጠገብ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ ገዳሙን የአቡነ በትረማርያም ረዳት በነበሩት በአቡነ በርተሎሚዮስ እንደተሠራ ይነገርለታል፡፡ በውብ አሠራር የተሠራ ድንቅ ቤተመቅደስ፡፡ በቅዱሳን ስዕላት የተዋበ፤ በእነዚያ ገዳማት ጥንታዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ጥሩር የተባለው አቡነ በትረማርያም ራሳቸውን ለማድከም ይለብሱት የነበረ፣ የነሀስ ከበሮና ሌሎች ቅርሶችን ይዘዋል፡፡
ጀንበር እያዘቀዘቀች ነው፡፡ የመመለሻዬ ጊዜ ግድ እያለ ነው፡፡ አይቼ ሳልጠግባቸው፣ እንደሳሰሁባቸው በቀጭኗ መንገድ ቁልቁል ወረድኩ፡፡ አካባቢው ነብስን ያድሳል፡፡ ጀልበዋ ልትመለስ ተዘጋጅታለች፡፡ ተጓዞች ሁሉ ገብተዋል፡፡ የመልስ ጉዞ ተጀምሯል፡፡
ʺአንቺ ቅድስት እና የአቤሜሌክ ሀገር
የግዮን መፍሰሻ የተመረጥሽ ምድር
ክብርና ሞገስሽ ይመለስልሻል
ቀድሞ ያከበረሽ መቼ ይተውሻል፡፡” ያ ግሩም ዝማሬ እየተንቆረቆረ ነው፡፡ አዎን ቀድሞ ያከበራት፣ አሁንም የሚጠብቃት፣ ነገም የማይተዋት አምላክ ኢትዮጵያን አይተዋትም፡፡ ዝማሬው ቀጥሏል፡፡ ጉዟችንም እንደዚያው፡፡
ʺከምድር ነገሥታት አንዳች አትጓጊ
ኢትዮጵያ እጆችሽን ወደ እግዚአብሔር ዘርጊ” የምድር ነገሥታት ገሚሶቹ ሲክዷት፣ ገሚሶቹ ደግሞ በዝምታ ሲመለከቷት፣ በጭንቋ ዘመን እጆቻቸውን ሲቀስሩባት ይኖራሉ፡፡ እርሱ ግን የዘረጋችውን እጇን በበረከት ይሞለዋል፤ ልመናዋን ይቀበለዋል፡፡ ምድሯን ሰላም ያደርገዋል፡፡ ጠላቷን ድል እንድትነሳ ያግዛታል፡፡ ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ መልካም ነው፣ እነሆም ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ እስከ አሮን ጢም፣ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። ጀልባዋ መልሕቋን ልትለቅ እየተቃረበች ነው፡፡ ጀንበርም መልካም ፈገግታ እያሳዬች ወደ መስኮቷ ልትገባ ደርሳለች፡፡ በየገዳማቱ የተበተነው ልቤ እየዋለለ ነው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ዘመቻው አሁንም እንደቀጠለ ነው” የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር
Next article“የኢትዮጵያ የውጭ እዳ ጫና በጠቅላላ ዓመታዊ እድገት አንፃር ሲታይ ከነበረበት 37 በመቶ ወደ 26 በመቶ ገደማ ወርዷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ