“በሱዳን እና ግብጽ በኩል ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቅም መርሆዎች ባፈነገጠ መልኩ የኢትየጵያን የውኃ የመጠቀም መብት ለመገደብ መሻታቸውና ጉዳዩን ዓለምአቀፋዊ ለማድረግ መጣራቸው የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም” በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ

168

“በሱዳን እና ግብጽ በኩል ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቅም መርሆዎች ባፈነገጠ መልኩ የኢትየጵያን የውኃ የመጠቀም መብት
ለመገደብ መሻታቸውና ጉዳዩን ዓለምአቀፋዊ ለማድረግ መጣራቸው የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም” በሱዳን የኢትዮጵያ
አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን ለሚገኙ
ልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዓባይ ተፋሰስ የኢትዮጵያን ሁለት ሦስተኛ የውኃ ሃብት የሚሸፍን እንዲሁም 86 በመቶውን ኢትዮጵያ የምታበረክት ቢሆንም ሃብቱ
እያለ እስካሁን ድረስ 65 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በኤሌክትሪክ እጦት በጨለማ ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡ አምባሳደሩ
ዓባይን ማልማት ለኢትዮጵያ መብቷ እና ግዴታዋ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የውኃ ሃብቷን ስትጠቀም ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ በመሆኑም በማንም ተጋሪ ሀገር ላይ ጉልህ ጉዳት
እንደማታደርስ ፣ ዓለምአቀፍ ሕግንና መርህን በማክበር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሱዳን፣ የጋራ ታሪክ ያላቸው ዕጣፈንታቸውም የተሳሰረ መሆኑን ያስረዱት አምባሳደር ይበልጣል በታሪክ እንደታየው
አንዳቸው ለአንዳቸው ጋሻ ሆነው መቆየታቸውን አውስተዋል። ከዚህ አንጻር ሱዳን ለኢትዮጵያውያን የክፉ ቀን መጠጊያ
እንደሆነችው ኹሉ ኢትዮጵያም ለሱዳን ሰላም፣ መረጋጋት እና አንድነት የቁርጥ ቀን ደራሽ መሆኗን አስታውሰዋል፡፡
በ1972 (እ.ኤአ.) በሰሜን እና ደቡብ ሱዳን ኃይሎች የሰላም ስምምነት እንዲመጣ ከማድረግ ጀምሮ በምሥራቅ አፍሪካ
የልማት በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ሥር በሰላም ሂደቱ ንቁ ሚና በመጫወት እንዲሁም በዳርፉር እና በአብዬ የሰላም
አስከባሪ በማሰማራት እስከ ህይወት መሰዋዕትነት መክፈሏን ጠቅሰዋል፡፡
አሁን በሱዳን ለተፈጠረው ሰላምና የሽግግር መንግሥት ምስረታ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሚና የሱዳን ሕዝብ
የሚያውቀው እንደሆነም አንስተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም ያለው በመሆኑም ሱዳናዊያን እና የሱዳን መንግሥት ለግድቡ ግንባታ
አስፈላጊውን የፖለቲካ፣ የቁሳቁስና የሞራል ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩ ጠቅሰዋል፡፡
ግድቡ የሱዳን ኃይል ማመንጫ ግድቦች ከዓመት እስከ ዓመት በሙሉ አቅማቸው ኃይል ለማመንጨት እንደሚረዳ፣ የዓባይ ወንዝ
ተመጣጣኝ ፍሰት ስለሚኖረው በዓመት ሦስት ጊዜ ለማምረትና ምርታማነትን እንደሚጨመር፣ ወደ ሱዳን ግድቦች ይገባ
የነበረውን ደለል በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ሱዳን ለደለል ማስወገጃ በየዓመቱ የምታወጣውን 50 ሚሊዮን ዩሮ እንደምታድን፣
በአነስተኛ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ማግኘት እንደምትችል፣ የጎርፍ አደጋ ሙሉ በሙሉ በማስወገድ
የህይወትና ንብረት ጥፋትን እንደሚታደጋት ገልጸዋል፡፡
ግድቡ ለሱዳን የሚሰጠው ጥቅም አሁን በስልጣን ላይ ያሉትን ጨምሮ በሱዳን ባለሙያዎች ጥናት የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ “ለ20
ሚሊዮን ሱዳናዊያን እና ለሱዳን ግድቦች አደጋ ነው” መባሉ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል፡፡
ከመረጃ ልውውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለማጋራት ዝግጁ መሆኗንና የግድቡን ሙሌት በተመለከተ
መቼ ምን ያክል ውኃ መያዝ እንዳለበት በሦስቱ ሀገራት ባለሙያዎች መግባባት የተደረሰበት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ ገንዘብ እና የራሷን ፍትሐዊ የውኃ ድርሻ ተጠቅማ ለምትገነባው ግድብ ውኃ አትሙላ ማለት ተቀባይነት የሌለው
መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ሱዳን እና ግብጽ አስገዳጅ የሚሉት ስምምነት ደግሞ አግላይ የሆነ፣ በግብጽ እና ሱዳን ብቻ የተደረገ ፍትሐዊ ያልሆነ የውኃ
አጠቃቀምና ክፍፍል የሚያስቀጥል እና ኢትዮጵያ በአባይ ውኃ ላይ ያላትን መብት የሚሽር እና ወደፊት የልማት ሥራ ከማከናወን
የሚገድብ ተቀባይነት የሌለው ሐሳብ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የግድቡ ጉዳይ በሦስቱ ሀገሮች መካከል በሚደረግ ድርድር የሚጠናቀቅ ኾኖ ሳለ በሱዳን እና ግብጽ በኩል ከድንበር ተሻጋሪ
ወንዞች አጠቃቅም መርሆዎች ባፈነገጠ መልኩ የኢትዮጵያን የውኃ የመጠቀም መብት ለመገደብ መሻታቸውና ጉዳዩን
ዓለምአቀፋዊ ለማድረግ መጣራቸው የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል አስታውቀዋል፡፡
በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ሥር በሚደረገው ድርድር ሦስቱን ሀገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት መድረስ እንደሚቻል
አምባሳደሩ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር በክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ፡፡
Next article“ዘመቻው አሁንም እንደቀጠለ ነው” የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር