“የግብር ሥራ ገንዘብ የመሠብሠብ ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን በመረዳት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ውጤታማ ግብር አሰባሰብ እንዲኖር ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ብዙዓየሁ ቢያዝን

295

“የግብር ሥራ ገንዘብ የመሠብሠብ ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን በመረዳት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ውጤታማ ግብር አሰባሰብ እንዲኖር ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ብዙዓየሁ ቢያዝን

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “ግብራችን ለኅልውናችን ” በሚል መሪ ሀሳብ የ2014 የበጀት ዓመት የደረጃ “ሐ” የግብር ከፋዮች የንቅናቄ መድረክ በእንጅባራ ከተማ ተካሂዷል።

በ2013 ዓ.ም በግብር አሰባሰብ የተሠራው ሥራ ጥሩ አፈጻጸም እንደተገኘበት ተመላክቷል፡፡ ለሥራው ስኬታማነት የግብር ከፋዮች ቅንነት ፣ የሥራ ኀላፊዎች ድጋፍ ፣ የግብር ማጭበርበር እንዳይኖር የቴክኖሎጂው ማደግ፣ ዜጎች ግብር እንዲከፍሉ የግንዛቤ ሥራ መሠራቱ፣ የገቢ ተቋም ሠራተኞችን ቁጥር ማደጉና የታክስ አምባሳደሮች መሰየማቸው በተሻለ መልኩ ግብር እንዲሰበሰብ ማስቻሉን በንቅናቄ መድረኩ ተጠቅሷል።

በ2013 የግብር ዘመን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 18 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ተሰብስቧል። ሙሉ በሙሉ እቅዱን ለማሳካት ደግሞ ክልላዊና ሀገራዊ ወቅታዊ ችግሮች እንደምክንያት ተገልጿል።

ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ የገቢ ተቋም ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርትና ኮምዩኒኬሽን የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አግማስ ጫኔ እንዳብራሩት በክረምት ወራት በግብር አሰባሰብ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር ፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ጎንደር ከተማ አስተዳዳር፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ታቦር፣ ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር፣ አዊና ሌሎች ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በአጭር ጊዜ የሚጠበቅባቸውን ግብር መሰብሰብ መቻላቸውን ጠቁመዋል።

እንደ ደቡብ ወሎ ያሉ ዞኖች ደግሞ አፈጻጸማቸው ደካማ በመኾኑ በቀጣይ ተጠናክረው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። የደረጃው”ሐ”ግብር ከፋዮች በቁጥራቸው በዛ ያሉ በመኾናቸው በአጭር ጊዜ ከፍለው እንዲያጠናቅቁና ለቀጣይ የግብር ሥራዎች በቂ ጊዜ ለማትረፍ ቀድሞ የንቅናቄ መድረክ መፈጠሩን ገልጸዋል።

በ2014 የግብር ዘመን ቢሮው ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች 650 ሚሊየን ብር ለመሠብሰብ እቅድ መያዙንም ተናግረዋል። 75 ሚሊየን ብር ከቤት ኪራይ እንደሚሰበሰብ ተገልጿል።

ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ የተገኙት ወይዘሮ ስንታየሁ ታፈረ ከተማ አስተዳደሩ የ2013 የግብር ዘመን የእቅድ አፈጻጸም ጥሩ እንደነበር በማስታወስ ክልሉ በ2014 ዓ.ም በእቅድ የያዘውን ገንዘብ እንዲሰበሰብ በስድስቱም ክፍለ ከተሞች የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተሠርቷል፤ ግንዛቤም ተፈጥሯል ፤የሥራ ስምሪትም ተሠቷል ብለዋል። ከሐምሌ አንድ እስከ ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም የደረጃ “ሐ” ግብርን መቶ በመቶ እንደሚሰበስቡም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ ብዙዓየሁ ቢያዝን እንደተናገሩት በባለፈው ዓመት ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በ15 ቀን ውስጥ 91 በመቶ ያለምንም ቅጣትና ወለድ ግብር መሠብሰብ ተችሏል፡፡ “ግብር ገንዘብ ብቻ የመሠብሠብ ጉዳይ አለመኾኑን በመረዳት በዚህ ዓመት በእቅድ የተያዘው ገንዘብ እንዲሰበሰብ ሁሉም ባለቤት ሊኾን ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ግብርን በብቃት መሰብሰብ እንደ ክልል ትልቅ ትርጉም የሚሠጠው ነው ያሉት ኅላፊዋ ጉዳዩም የኅልውና ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ለማኀበረሰቡ የሚሰጠውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግልጋሎት ለማሳካት ግብር ጠንክሮ መሠብሰብ እንደሚገባም ተናግረዋል። ቢሮው ለግብር ከፋዮች የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ :- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ሳያቋርጡ እያከናወኑ እንደሚገኝ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next article“በደግነታቸውና ወደር በሌለው አዛኝነታቸው የሚታወቁት የአበበች ጎበናን ዜና ረፍት በከፍተኛ ሐዘን ነው የስማሁት” ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ