የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በንቅናቄ ሲሠሩ የቆዩ ሥራዎች በሚፈለገው መልኩ ውጤት አለማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡

86
የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በንቅናቄ ሲሠሩ የቆዩ ሥራዎች በሚፈለገው መልኩ ውጤት አለማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከግንቦት 10/2013 ዓ.ም ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የንቅናቄ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገም ኢንስቲትዩቱ ከየዞኑ ከመጡ የሥራ ኀላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ግምገማዊ ውይይት በባሕር ዳር እያካሄደ ነው።
አቶ ደምሌ ካሳ በሰሜን ወሎ ዞን የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪ ናቸው። በሰሜን ወሎ ዞን ከከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ የኅብረተሰብ ንቅናቄ በማከናወናቸው ኮሮናቫይረስን ከመከላከል አንፃር የተሻለ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በንቅናቄው በዞኑ 96 ሺህ አባወራዎችን ተደራሽ በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ማከናወናቸውን አስረድተዋል። በዞኑ ፈጣን የኾነ የምርመራ ክፍል ማቋቋማቸውን አቶ ደምሌ ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ ተመሥገን አንተዬ በክልሉ 93 በመቶ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለመስጠት መቻሉን ተናግረዋል። በክልሉ እስከ አሁን ለ408 ሺህ 801 ሰዎች የመጀመሪያው ዙር ክትባት ተሰጥቷል፤ እስካሁን ለ1 ሺህ 313 ሰዎች ደግሞ የሁለተኛ ዙር ክትባት መስጠት እንደጀመሩ ባለሙያው አስረድተዋል።
“በአጠቃላይ በንቅናቄው የተሠሩ ሥራዎች ዝቅተኛ ስለኾኑ ወረርሽኙ ደግሞ ገዳይነቱን የቀጠለ በመሆኑ አመራሩና ባለሙያው በቀሪ ጊዜያት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል” ነው ያሉት አቶ ተመሥገን፡፡
የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት “ዳግም ትኩረት ለኮሮናቫይረስ” በሚል ሐሳብ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በንቅናቄ በተከናወነ ሥራ 1 ሚሊዮን 781 ሺህ በላይ የቤት ለቤት የአሰሳ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ 364 ሺህ 826 የቤት ለቤት አሰሳ መደረጉን አስታወቋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት በተከናወኑ የንቅናቄ ሥራዎች ወረርሽኙን ከመከላከል አንፃር ሰሜን ወሎ ዞን የተሻለና ሥራውንም 60 በመቶ አከናውኗል፤ ሌሎች ዞኖች ግን ሥራቸውን ያልጀመሩ አሉ ብለዋል።
በዘመቻው በቀን 5 ሺህ 165 ሰዎችን ለመመርመር ታቅዶ በአጠቃላይ 7 ሺህ 145 ሰዎች ብቻ እንደተመረመሩ ተናግረዋል።
በመንግሥት ተቋማት “እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ (No Mask, No Service)” ተግባራዊ በማድረግ በኩል የተዋቀረው ግብረኀይል በአግባቡ እንዳልሠራም ጠቁመዋል።
የወረርሽኙ መጨመርና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የተዛባ አመለካከት ደግሞ ሠፊ በመኾኑ እቅዱን ለማከናወን ተግዳሮት እንደኾነባቸው ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት ራሳቸውን ችለው የኮሮናቫይረስ ምርመራና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ሕሙማን የኮሮናቫይረስ ምልክት ከታየባቸው የቀጥታ ምርምራ ሥራን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
“በየዞን ከተሞች ከሚሰጠው የምርመራ ሥራ በተጨማሪ በ22 ሆስፒታሎችና በሌሎች የጤና ተቋማት የቀጥታ ምርመራ እንዲደረግ ቢታቀድም የጤና ባለሙያዎች ኮሮናቫይረስን እንደ ሌሎች በሽታዎች አይቶ ሊያከናውኑ አልቻሉም” ብለዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል ከወረዳ እስከ ቀበሌ የተዋቀረው ግብረኀይል ሥራውን በአግባቡ ሊያከናውን እንደሚገባም አቶ በላይ አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የኢትዮጵያ የርህራሄ ተምሳሌት የነበሩት አበበች ጎበናን ህልፈተ ህይወት ስሰማ እጅግ አዝኛለሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየአካባቢያቸዉን ሰላም ለማስጠበቅ ሲሉ ሕይወታቸውን ላጡ የፓሊስ፣ የሚሊሻ እና የልዩ ኀይል ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የዋግ ልማት ማኀበር አስታወቀ።