
“ፖሊስነት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅምና ክብር ሲባል ራስን አሳልፎ በመስጠት መስዋእትነት የሚከፈልበት ክቡር ሙያ ነው”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 27/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ልዩ መደበኛ ምልምል ፖሊሶችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ለ1ኛ ዙር ልዩ መደበኛ ምልምል ፖሊሶች መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አንማው አለሜ ወቅቱ የሥነልቦና ዝግጅት እና የአካል ብቃት የሚጠይቅ በመሆኑ የጸጥታ አካላት ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል። ከምንጊዜውም በላይ እርስ በእርስ በመግባባት ሀገርን እና ሕዝብን ማዳን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

“ፖሊስነት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅምና ክብር ሲባል ራስን አሳልፎ በመስጠት መስዋእትነት የሚከፈልበት ክቡር ሙያ ነው” ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ። ተመራቂዎች በተሰማሩበት የሙያ መስክ የክልሉን ሰላም በመጠበቅና ለሀገራችን እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ በአመለካከት እና በሥነምግባር ጠንካራ አቋም በመያዝ በገቡት ቃል መሰረት የጸጥታ አካላት ሕብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ተመራቂዎችም በተሰጣቸው ስልጠና ብቁ መሆናቸውንና በገቡት ቃል መሠረት ወንጀልን ለመከላከል በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ እና መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ – ከደብረ ማርቆስ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ