ከጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቶች 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ።

212

ከጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቶች 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ።
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላኩ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቶች 140 ሚሊዮን
የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ የ2013 በጀት ዓመት የ11 ወር ዕቅድ አፈጻጸሙን በደብረ ብርሃን ከተማ በተወያየበት ወቅት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ
ስለሺ ለማ እንዳሉት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፉን ውጤታማነት ለማስፋፋት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተገንብተው ወደ ሥራ
ገብተዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ባለፉት 11 ወራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የፈጠረውን ጫና ተቋቁመው
ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ አቅርበው 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
የምርቱ መዳረሻዎች አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቱርክ፣ ጣልያን እና ጀርመን መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በኮሮናቫይረስ
ወረርሽኝ ምክንያት 90 በመቶ የነበረው የውጭ ገበያ አቅርቦት ወደ 60 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል።
የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን በማዘመንና ጥራትን በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘንድሮ በመስኩ ምሁራን 22 ጥናትና
ምርምሮች ተደርገው 11ዱ ተጠናቀው ለባለድርሻ አካላት እንዲደርሱ መደረጉን ጠቁመዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በ2013/2014 የምርት ዘመን የዘርፉን የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ለማቃለል በ150 ሺህ
ሄክታር መሬት ላይ 170 ሺህ ቶን ጥሬ ጥጥ ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው።
የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ተመራማሪዎች የበኩላቸውን እገዛ በማድረግ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም
መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ ፍተሻ ባለሙያ ወይዘሪት ሰላም ገበየሁ በበኩላቸው “ኢንስቲትዩቱ በማማከር፣ በጥናትና ምርምር
እንዲሁም በውጭ ሀገር የገበያ ትስስር መፍጠር ባለሃብቶችን ይደግፋል” ብለዋል።
በቀጣይ ሀገሪቱ በዘርፉ የተሻለ ገቢ እንድታገኝና ባለሃብቶችም ምርታማነታቸው እንዲጨምር ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“በተመረቅንበት የሙያ መስክ ሕዝባችንን ለማገልገል ቁርጠኞች ነን” ተመራቂ ተማሪዎች
Next articleበአዲስ አበባ ከተማ የአማራ ወጣቶች ማኅበር በአጣዬ እና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ፡፡