
“የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለዜጎች ክብር ያለው አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል” ሰላም ሚኒስቴር
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለዜጎች ክብር ያለው አገልግሎት በመስጠት
ለዘላቂ ሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ
ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ተኮር የከፍተኛ አመራር አባላት የውይይት መድረክ በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ዛሬ በአዲስ
አበባ ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለጹት፤ በመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ በሚሰጡ አገልግሎቶች እርካታ
መፍጠር እንደ ሀገር ለተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት አስተዋጽዖ አለው።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮች በጥናት መለየታቸውን ጠቁመው፤ ከተለዩት
ጉዳዮች መካከል የሀገረ መንግሥትና የብሔረ መንግሥት ግንባታ አለመጠናቀቅ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ ሁለት አንኳር ጉዳዮች ለዘላቂ ሰላም መሳካት ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል። የሀገረ መንግሥት ግንባታን ለማጠናቀቅ
ጠንካራ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፤ “ከግለሰብ ጀምሮ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና በተቋም ደረጃ
የሚረጋገጥ ሰላም አስፈላጊ ነው” ብለዋል። ብቃት ያለው፣ አገልጋይ፣ በእውቀትና ክህሎቱ የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሰ የሰው ኀይል
እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ይህም የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት ምላሽ ሰጪነት አቅም እንደሚያሳድግ ተናግረዋል። የተቋማትን አሠራር በአደረጃጀት፣
በቴክኖሎጂ ማዘመንና ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለዜጎች ክብር ያለው አገልግሎት መስጠታቸውን ማረጋገጥ መቻል እንዳለባቸው
አመልክተዋል።
ይህም በዜጎችና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን የተሻለ ደረጃ ላይ በማድረስ ለተጀመረው የዘላቂ ሰላምና የዴሞክራሲ
ሥርዓት ግንባታ መጎልበት የራሱ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የሲቪል ሰርሺስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ በበኩላቸው ሰላምና የመንግሥት አገልግሎት ቁርኝታቸው የጎላ መሆኑን
ገልጸዋል። በመንግሥት አገልግሎት ዘርፎች ሁሉ ቅድሚያ ለዜጎች ክብር ምላሽ ሊሰጥ በሚችል አደረጃጀት በተናበበ መልኩ
መሥራት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።
“አገልግሎት በነፃነት፣ በገለልተኝነትና በሙያ ብቃት የሚሰጥ ከሆነ ዜጎች የአገልግሎት እርካታ ስለሚያገኙ ሰላማቸውን
በባለቤትነት ይጠብቃሉ” ብለዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m