
“የእሳት አደጋ መከላከል ሥራው በዙሪያው ላሉ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች እና ተቋማት አገልግሎት መስጠት በሚችልበት ቁመና
መደራጀት አለበት” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር)
የባሕር ዳር ኢንዱስትሪያል ፓርክ ላለፉት ሦስት ወራት ያሰለጠናቸውን የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች አስመርቋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው ጥቅምት ወር መግቢያ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው ባሕር ዳር ኢንዱስትሪያል
ፓርክ ላለፉት ሦስት ወራት ያሰለጠናቸውን 25 የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች አስመርቋል፡፡ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ
ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከተገነቡት 13 ኢንዱስትሪያል ፓርኮች መካከል የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ ነው፡፡
ኢንዱስትሪያል ፓርኩ 8 ሸዶች ያሉት ሲሆን ሆፕ ሉን የጨርቃ ጨርቅ ድርጅት የሙከራ ምርት ሂደቱን አጠናቆ ወደ ማምረት ሂደት
ተሸጋግሯል፡፡
ዛሬ ከተመረቁት 25 የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች መካከል 12 በልማት ተነሽ ከሆኑት አርሶ አደሮች ቤተሰብ የተመረጡ
ናቸው፡፡ የባሕር ዳር ኢንዱስትሪያል ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጥሩየ ቁሜ በቀጣይም ፓርኩ ለአካባቢው ማኅበረሰብ
የሥራ እድል በመፍጠር በኩል መልካም አጋጣሚ ይሆናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በመላ ሀገሪቱ 13 ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን በመገንባት ወደ ሥራ እያስገባ
ነው ያሉት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፓሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን እስካሁን ባለው
ሂደት 86 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት፡፡
በኢንዱስትሪያል ፓርኮቹ መገንባት ምክንያት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችም ወደ
200 ሺህ እንደሚደርሱ ነው ምክትል ሥራ አስፈጻሚው የጠቆሙት፡፡
በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር) ሙያዊ ስልጠናው
ከኢንዱስትሪያል ፓርኩ አልፎ ለባሕር ዳር ከተማ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡ የእሳት አደጋ መከላከል ሥራው ከከተማዋ አልፎ
በዙሪያው ላሉ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች እና ተቋማት አገልግሎት መስጠት በሚችልበት ቁመና መደራጀት እንደሚገባውም
ተናግረዋል፡፡
ሰልጣኞቹ በበኩላቸው ላለፉት ሦስት ወራት ከፊል ወታደራዊ፣ የእሳት አደጋ መከላከል እና ፈልጎ ማግኘት ሙያዎች ላይ በቂ
ሥልጠና እና ልምድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለመስጠትም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፓርኩ ሠራቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው
እንግዶች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በፓርኩ ቅጥር ግቢ ሀገር በቀል ችግኞችን ተክለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m