መምህራን የተማሪዎችን ውጤትና ሥነ ምግባር በማሻሻል ላይ ትኩረት ሊሠጡ እንደሚገባ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አሳሰበ።

321

መምህራን የተማሪዎችን ውጤትና ሥነ ምግባር በማሻሻል ላይ ትኩረት ሊሠጡ እንደሚገባ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አሳሰበ።

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዛሬ በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሃ ግብሮች ያሠለጠናቸውን 1 ሺህ 592 ተማሪዎች አስመርቋል።
የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ በአማርኛ፣ በአዊኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋ በማሠልጠን ውጤታማ መምህራንን እያፈራ መሆኑን የኮሌጁ ዲን ሽቱ አየነው ተናግረዋል።
መምህርነት የተከበረ ሙያ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሽቱ እጩ ተመራቂዎችም ሙያው የሚፈልገውን ሥነ ምግባር በመላበስ ሀገር ማገልገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ለዚህም በኮሌጅ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር መለወጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት የትምህርት ጥራት ችግር አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት ሀገር ተረካቢ ህጻናትን በብቃት ማስተማር ይገባቸዋልም ብለዋል።
ኮሌጁ 271 ወንድ እና 821 ሴት እጬ መምህራንን ማስመረቁ ተገልጿል። ባለፉት 11 ተከታታይ ዓመታት 24 ሺህ 403 መምህራንን ማሠልጠኑንም ተናግረዋል።
ይህም በዘርፉ የሚታየውን የመምህራን እጥረት እየቀረፈ ነው ብለዋል። “ሰርቶ ያልደከመ ወጣት ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የለውጡ ባለቤት በመሆን ለሰላም ዘብ መቆም አለበት” ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ወንደሰን አቤ እንደተናገሩት በክልሉ በባለፉት ዓመታት ሁሉም ዜጎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
ትውልድ ለመቅርጽ የመምህራን ሚና ላቅ ያለ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው በዕውቀትና በጥራት ብቁ መምህራንን ለማቅረብ ክልሉ እየሠራ ነው ብለዋል። መምህራን የተማሪዎችን ውጤትና ሥነ ምግባር በማሻሻል ላይ ትኩረት ሊሠጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከ10 ዓመታት በፊት በክልሉ በአራት የመምህራን ኮሌጆች ለመጀመሪያ ደረጃ መምህራን ስልጠና ሲሠጥ የነበረ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በአሁኑ ጊዜ በ10 ኮሌጆች ስልጠና እየተሠጠ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ ኮሌጆች በአሁኑ ጊዜ ከ70 ሺህ በላይ መምህራንን ተቀብለው እያስተማሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ተማሪዎች ወደ ተግባር ሲገቡም የአንጋፋ መምህራንን ልምድ ተከትለው ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል። እጩ ተመራቂ መምህራን በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፅናት በመቋቋም ሀገር ተረካቢ ህጻናትን በጥሩ ስዕብና መገንባት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ተመራቂዎች በኮሌጅ ከአገኙት ዕውቀት በተጨማሪ በየጊዜው ለማንበብ ዝግጁ መሆን አለባቸውም ብለዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ባይነሳኝ ዘሪሁን መምህራን ዘመናዊ አሠራር እንዲስፋፋና እድገት እንዲመጣ ላቅ ያለ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል። በብሔረሰብ አስተዳደሩ ለትምህርት የደረሱ ህጻናት የትምህርት ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታም እየሰፋ መሆኑን ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት አንድነትን በማጠናከር ላይ እንገኛለን” ያሉት አቶ ባይነሳኝ እጬ መምህራንም ለዚህ ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከፍተኛ ውጤት ከአስመዘገቡ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ማንችሎበት የትነበርህና ማዛ ገብሩ እንደገለጹት የኮሮና ወረርሽ የትምህርት አሰጣጡን ቢያስተጓጉልም የራሳቸውን ተነሳሽነት በማጠናከር ለጥሩ ውጤት መብቃታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይም በተማሩት ሙያ በትጋት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሠራዊቱ ለሕግና ለሞራል የሚገዛ በመሆኑ በሕዝብ ላይ ከመተኮስ መስዋእትነትን መርጧል” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ
Next article“የእሳት አደጋ መከላከል ሥራው በዙሪያው ላሉ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች እና ተቋማት አገልግሎት መስጠት በሚችልበት ቁመና መደራጀት አለበት” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር)