
ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) በእንስሳት ልማት ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማ ለመሆን ዓላማ ያደረገ የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። በውይይቱም በአማራ ክልል የሚገኙ 22 የወተት፣ የስጋና የእንቁላል እንስሳት መኖ አምራቾች፣ በእንስሳት ዙሪያ የሚሰሩ አጋር አካላትና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱም ዘመናዊ የአረባብ መንገድን ያልተከተለ የእንስሳት አያያዝና አመጋጋብ፣ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ እንስሳት ዝርያዎች በስፋት አለመኖርና የእንስሳት በሽታዎች መኖር የዘርፉ ፈተዋናዎች እንደሆኑ ተነስቷል።
የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈንቴ ቢሻው ክልሉ በሚፈለገው ልክ ከእንስሳት ሀብቱ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ጠቅሰው ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ዘርፉን ለማሳደግም የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል የሚያስችል ናይትሮጅን በአምስት ዞኖች እየተመረተ እንደሆነና ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ በክልሉ 140 የተዳቀሉ ጥጃዎች መወለዳቸውን አስረድተዋል። 30 ሺህ 891 ቶን የተቀነባበረ የእንስሳት መኖ መገኘቱንም ተጠቁመዋል።
የስጋና የእንቁላል ጣይ ደሮዎችን ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ ከ341 በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶችን የሚያከፋፍሉ ኢንተርፕራይዞች እንዳሉም አመላክተዋል።
በእንስሳት ሀብት ልማቱ የሚታዩ ችግሮችን እየተከታተሉ ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጡና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያሳዩ የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት የክብር አምባሳደሮችም ተመርጠዋል።
ዶክተር ተሾመ ዋለ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ፣ ዶክተር ዘውዱ ውለታው ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት፣ ዶክተር ተቀደሰ ያየህ ከባሕር ዳር ዩኒሸርሲቲና በግል የሥራ ዘርፍ የተሰማሩት ዶክተር አወቀ ኪዳነማርያም አምባሳደር ሆነው ተመርጠዋል። ግለሰቦቹ ያላቸው የካበተ የሥራ ልምድ ለክልሉ እንስሳት ሀብት ዕድገት ይጠቅማል በሚል ነው የተመረጡት።
የአማራ ክልል አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የቁም እንስሳት ሀብት ባለቤት መገኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። በዓመት 1 ቢሊዮን 217 ሺህ ሊትር ወተት፣ 495 ሺህ ቶን ስጋ፣ 535 ሚሊዮን እንቁላል የማምረት አቅም እንደለውም ከክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ፦ ኃይሉ ማሞ