አሸባሪው ሕወሓት እርዳታ በአውሮፕላን እንዲገባ በመጠየቅ የሚፈልጋቸውን የጦር መሳሪያዎች ለማስገባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገለጸ።

443

አሸባሪው ሕወሓት እርዳታ በአውሮፕላን እንዲገባ በመጠየቅ የሚፈልጋቸውን የጦር መሳሪያዎች ለማስገባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገለጸ።

ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉብርሃን ኃይሌ እንደተናገሩት አሸባሪው ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ወደ ጦርነት እንዲገባ እየቀሰቀሰ ይገኛል።

“አሸባሪው ሕወሓት ሀገርን የማተራመስና የማፍረስ እኩይ ተግባር እያከናወነ ይገኛል። የተከዜን ድልድይ ጨምሮ በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ ሕዝብ ሀብት የተገነቡትን መሰረተ ልማቶች በማውደም ላይ ይገኛል” ሲሉ ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብን በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ዋጋ በማስከፍል ወደ በለጠ ችግርና ሰቆቃ እየከተተው በመሆኑ የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጉዳዩን በአግባቡ መረዳት እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

በፖለቲካና በጦርነት የተሸነፈው አሸባሪው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ጥያቄ የመመለስም ሆነ የማስተዳደር አቅም እንደሌለው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ “መሰረተ ልማቶችን በተለይም ድልድይ በማፈራረስ ትርፍ ለማግኘት እየሞከረ ነው” ብለዋል ።

ሕወሓት መሰረተ ልማትና ድልድይ የሚያፈርስበት ለሁለት ዓላማ ነው ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ አንደኛው የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የሚያቀርቡትን እርዳታ ለትግራይ ሕዝብ እንዳይደርስ በማድረግ “በረሃብ ሊጨርስህ ወስኗል” በሚል ፕሮፓጋንዳ ወደ ራሱ ለማሰለፍ አልሞ መሆኑን አመልክተዋል።

ሁለተኛው ደግሞ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ድልድዮች ስለተሰበሩ ወደ “ትግራይ እርዳታ መግባት አይችልም” በሚል ምክንያት፤ “እርዳታ በአውሮፕላን እንዲገባ በመጠየቅ የሚፈልጋቸውን የጦር መሳሪያዎች በማስገባት” የጀመረውን ሀገር የማፍረስ እኩይ ተግባሩን አጠናክሮ ለመቀጠል እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና ፓርቲያቸው ይሄን የሚያስደግፍ መረጃ አግኝቷል በማለት ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ክልል ወጣቶች እየተሰደዱ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሙሉብርሃን ምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማያደርጉ ወጣቶችን የብልጽግና፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አረና አባላት ናችሁ በሚል እያሰቃየ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ትግራይን ማስተዳደርና የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እንደማይችል ያውቃል ነው ያሉት የትዴፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው። በዚህም አመጽ እንደሚነሳበት ስለሚያውቅ ሕዝቡን ወደ ጦርነት ለመክተት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው አሸባሪው ሕወሓት በአውሮፕላን እርዳታ ይቅረብ በሚል ሰበብ የጦር መሳሪያ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ እቅድ አለው በሚል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ያቀረበው ሐሳብ መረጃ ተገኝቷል።

በአሁኑ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ የሚደርስባቸውን መጋቢ መንገዶችና ድልድዮች ላይ ጉዳት በማድረስ እርዳታ በየብስ ትራንስፖርት እንዳይገባ መስተጓጎል እየፈጸመ እንደሆነ ለማወቅም ተችሏል።

ለትግራይ ሕዝብ እርዳታ አልደረሰም ሕዝቡ በረሃብ ሊሞት ነው በሚል ሰበብ በአውሮፕላን እርዳታ ይላክ በሚል በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ዓለም አቀፍ ጫና በማሳደር በእርዳታ ሽፋን የጦር መሳሪያ ለማስገባት ጥረት የማድረግ እቅድ እንዳለው ነው ምንጮቹ የገለጹት።

ሕወሓት “በዓለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ የሚያደርጉለትን ማርቲን ፕላውት፣ጄቲል ትሮንቮል፣አሌክስ ዴ ዋል፡ዊሊያም ዳቪሰን፣ራሺድ አብዲ፣አወል አሎና ሌሎች ቅጥረኞቹን በመጠቀም ዘመቻ መከፈቱን ነው” መረጃዎች የሚያመላክቱት።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleኢትዮጵያና ስዊድን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
Next article“ኢትዮጵያ ዘንድሮ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ የቻለችው ሁላችንም ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ በመሥራታችን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ