ኢትዮጵያና ስዊድን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።

141

ኢትዮጵያና ስዊድን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 25/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒ ሊንድ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የስልክ ውይይት አድርገዋል።

ኢትዮጵያና ስዊድን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል የቆየውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም አቶ ደመቀ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊነት በማስቀደም በትግራይ ክልል የሚከሰተውን የሰብዊነት ቀውስና የኢኮኖሚ ውድመትን ለማስቀረት የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን አስረድተዋል፡፡

የህወሃት ሽብር ቡድን በተመሳሳይ ከጠባ ጫርነት በመታቀብ ግጭት እንዲያቆምና ለክልሉ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር በተባበር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ለክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ከረድኤት ድርጅቶች ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን በመጥቀስ፤ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ ደመቀ ጠይቀዋል፡፡

ስድሰተኛው ሀገራዊ ምርጫም ሰላማዊና ስኬታማ በሆነ መልኩ የተጠናቀቀ መሆኑንም አብራርተውላቸዋል፡፡ በምርጫ ዉጤት መሰረት የሚቋቋመው አዲስ መንግሥት መመሥረት ጎን ለጎን በሀገሪቱ ሁሉንም የሚሳተፍበት ውይይቶች በፌዴራል እና ክልሎች ደረጃ ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት በሚካሄደው ብሔራዊ ውይይቶች ትኩረት እንደሚሰጥበት ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ በበኩላቸው መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ መውሰዱን አድንቀዋል፡፡ በቀጣይም በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን እና በክልሉ የተፈጠረው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሚመለከተው አካላት በማጣራት እርምጃ እንዲወሰድ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ እና የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሚኒስትሯ ላነሱት ጥያቄ፤ የኢትዮ-ሱዳን ድንበርን በተመለከተ ሱዳን ከያዘቻቸው ቦታዎች ለቃ እንዲትወጣ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ እየተደረገ መሆኑን ተገልጾላቸዋል፡፡

አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ከሱዳን ጋር ጉዳዩን ለመፍታት በተቀመጡ አሠራሮች መሠረት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝ ፍላጎት መሆኑን አቶ ደመቀ አብራርተዋል፡፡

የህዳሴ ግድብን ድርድርን በተመለከተ የሱዳንና ግብፅ ወገን አለም አቀፋዊና ፖለቲካዊ በማድረግ ለተባበሩት መንግስታት የሚወስዱት አካሄድ አግባብነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ መፍትሔ እንዲሰጠው በውሃ ሙሌት በተመለከተ በየምዕራፎች ድርድር እንዲደረግ የኢትዮጵያ አቋም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሯም የህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት መፍትሔ እንዲሰጠው የሚደግፉ መሆኑን ጠቁመው፤ የስዊድን መንግሥት በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሥራዎች ለመደገፍ እና ሌሎች ትብብሮች አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ነው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ 100ኛ የምስረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
Next articleአሸባሪው ሕወሓት እርዳታ በአውሮፕላን እንዲገባ በመጠየቅ የሚፈልጋቸውን የጦር መሳሪያዎች ለማስገባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገለጸ።