
“መንግሥት የሕግ ማስከበር ግዳጁን በብቃት በመወጣት አጀንዳውን ወደ ሌላ ቀዳሚ ተልዕኮ ማድረጉ የተሻለ ወታደራዊ ስልት ነው” በውትድርና ኢትዮጵያን ያገለገሉ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል መንግሥት የሕግ ማስከበር ግዳጁን በብቃት በመወጣት አጀንዳውን በሀገራዊ ቀዳሚ ተልዕኮ ላይ ማድረጉ የተሻለ ወታዳራዊ ስልት መሆኑን ለረጅም ዓመታት በውትድርና ሙያ ኢትዮጵያን ያገለገሉ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ገለጹ።
ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማሪያም በቀደሙት ዘመናት በአየር ወለድ አባልነት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሰልፈው ኢትዮጵያን በውትድርና አገልግለዋል፡፡ ”ወትሮውኑ መንግሥት ወደ ትግራይ የገባው ክልሉን በሞግዚትነት ለማስተዳደር አይደለም” ይላሉ።
የመንግሥት ሠራዊት ወደ ትግራይ ሲገባ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነውን ግልጽና የቅርብ አደጋን ለመቀልበስ መሆኑ መረሳት እንደሌለበት ነው አጽንኦት የሰጡት።
እስካሁንም መንግሥት ባለፉት ስምንት ወራት ሲያካሂድ የቆየው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ግቡን የመታ መሆኑም መታዘብ እንደሚቻል አብራርተዋል።
በዚህ ወቅትም መንግሥት የስልት ለውጥ ማድረጉ ትክክለኛና ተገቢ ውሳኔ መሆኑን ነው ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ የገለጹት።
“ወታደራዊ ስልት በባህሪው ግትር አይደለም፤ ስልት ከሁኔታዎች ጋር ተለዋዋጭነት ባህሪ ያለው ነው” ብለዋል።
”መንግሥት ቀዳሚ አጀንዳዬ ነው’ ብሎ የጠቀሰውን ሁለተኛው ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ማካሄድና መደበኛ የክረምት ግብርና ሥራ ላይ ማተኮሩ ተገቢ እንደሆነ አመልክተዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ እንዳሉት በዚህ ወቅት ሠራዊቱ የቦታ ለውጥ ማሻሻያ በማድረጉ አሸባሪው ሕወሓት ከቁጥጥሩ ውጪ እንደሆነ ማስመሰል ተገቢ አይደለም። ይልቁንስ በቀጣይ ሊቃጡ የሚችሉ ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችል ቁመና እንዲገነባ ያስችለዋልም ነው ያሉት።
ሌላው የቀድሞ አየር ወለድ አባል ኮሎኔል ታምሩ ኃይሉ እንደሚሉት የአሸባሪዎች ዓላማ የመንግሥትን አጀንዳ ማስጣልና ራሱ በቀየሰለት መንገድ እንዲጓዝ ማድረግ ነው። መንግሥት ይህን ዓላማ ዋጋ በማሳጣት በራሱ አጀንዳ ለመሄድ መወሰኑ ትክክለኛ አቅጣጫ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ሥራ በመሥራት ሕዝቡን ሲያደናግር መቆየቱንም ጨምረው ይገልጻሉ። በዚህም ”ሳይገድሉ ገደልን በማለት በሕዝቡ ላይ የሥነ ልቦና ጫና ማድረግና በጉልበት ለውጊያ ማሰለፍን ይጠቀማል” ብለዋል። ይህ ሁኔታ ሲከሰት መንግሥት ለቆ መውጣትና በመደበኛ አጀንዳው ላይ ማተኮር ተገቢ እርምጃ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የሽብር ሌላው አስከፊ ገጽታ ሸማቂዎች ከንጹሐን ዜጎች ጋር ተመሳስሎ የተደራጀ ሠራዊትን መተንኮስና ማጥቃቱ መሆኑንም አብራርተዋል ኮሎኔል ታምሩ።
መንግሥት የሕግ ማስከበር ግዳጁን በብቃት በመወጣት አጀንዳውን ወደ ሌላ ቀዳሚ ተልዕኮ ማድረጉ የተሻለ ወታደራዊ ስልት ነው ሲሉም በውትድርና ኢትዮጵያን ያገለገሉ ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ ገልጸዋል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ