
ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ባሕር ዳር: ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቹንግ ኢዩ ዮንግ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የስልክ ውይይት አድርገዋል።
ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረና በደም የተሳሰረ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ደመቀ በሀገራቱ መካከል የቆየውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ተግባራት ለማሳለጥና የክረምት ወቅት በመሆኑ ማኅበረሰቡን የእርሻ ሥራውን ተረጋግቶ እንዲያከናውን የተናጥል የተኩስ አቁም ማወጁን ተናግረዋል። ይህ የመንግሥት እርምጃ በአንዳንድ አካላት ይነሳ የነበረውን ስጋት በመቅረፍና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ አካላት ሥራቸውን በተመቻቸ ሁኔታ እንዲሠሩ ለማስቻል ሊረዳ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በኢትዮጰያ ለሰብዓዊ ድጋፍ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይሄው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ማካሄዷን በመጥቀስ በአሁኑ ወቅትም የምርጫ ውጤቱ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ገልጸውላቸዋል።
በውይይታቸው ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በብዙ ዘርፎች ከማጠናከር ጎን ለጎን በባለብዙ መድረኮችም መደጋገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቹንግ ኢዩ ዮንግ በበኩላቸው የሀገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊነትን በማስቀደም በተናጥል ያወጀውን የተኩስ ማቆም ውሳኔ እንደሚደግፉ ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ ያካሄደችው ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና በዓለም አቀፍ መድረኮችም በጋራ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
ደቡብ ኮሪያ በቀጣዩ ዓመት ታኅሣሥ ላይ ለምታካሂደውና ትኩረቱን በመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ዘመቻ ላይ በሚያደርገው ስብሰባ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥሪም ተቀባይነት ማግኘቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ