የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ለአንበጣ መንጋ መከላከል ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ፡፡

105
የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ለአንበጣ መንጋ መከላከል ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጋዛጊብላ ወረዳ በሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገልጿል፡፡
በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ በዛብህ ጌታሁን እንዳሉት የአንበጣ መንጋው ከሰኔ 23/2013 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ በጋዝጊብላ ወረዳ በሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች ቢከሰትም በሁለቱ ቀበሌዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ማኅበረሰቡን በማስተባበር መቆጣጠር ተችሏል፡፡ በሌሎች ቀበሌዎች በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራው እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ወደ ሌሎች ወረዳዎች እንዳይዛመትም የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ እስከ አሁንም አንበጣው ካረፈበት እፅዋት ውጭ በሰብል ላይ ጉዳት አለመድረሱ በሁለት ቀበሌዎች ላይ በመገኘትና ከባለሙያዎች ባገኙት ሪፓርት ማረጋገጣቸውን ቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡
አንበጣ መንጋው በሰሜን ወሎ ዞን በኩል አድርጎ መግባቱንም ነው ቡድን መሪው የገለጹት፡፡ አሁንም ተጨማሪ የአንበጣ መንጋ ወደ አካባቢው እንዳይዛመት ክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
ቡድን መሪው በሰብል ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ቢገልጹም የጋዝጊብላ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ሶሎሞን ማእዛ ቀድመው በደረሱ በገብስ እና በማሽላ ሰብሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ከቦታው ተገኝተው ማረጋገጣቸውን ነግረውናል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ አንበጣ መንጋው ከሰኔ 20/2013 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሞ እና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደሮች እንዲሁም በሰሜን እና በደቡብ ወሎ ዞኖች በሚገኙ 14 ወረዳዎች መከሰቱን ገልጸዋል፡፡
የአንበጣ መንጋው ከአፍር ክልል እንደተነሳም ነው አቶ አለባቸው የገለጹት፡፡ መንጋውን በባሕላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል፡፡ የኬሚካል መርጫ መሳሪያ እና አልባሳት በኮምቦልቻ መቅረቡን አቶ አለባቸው ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሠረት ማኅበረሰቡን በማስተባበር የመከላከል ሥራ ለመሥራት የቅድመ ዝግጅት ተግባር መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበተያዘው ክረምት ከ14 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኝ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleወይዘሮ ኢትዮጵያ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ 2 ሺህ ዶላር ለገሱ፡፡