
በተያዘው ክረምት ከ14 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኝ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር መለሰ አስፋው በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ የቀበሌ 08 ነዋሪ ናቸው፡፡ ኑሯአቸውን የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በማዘጋጀት እና በመሸጥ ይመራሉ፡፡ ወደ ሥራው የገቡት ከሰባት ዓመት በፊት በቆቦ ጊራና የተቀናጀ የመስኖ ፕሮጀክት ተቀጥረው ሲሠሩ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ነበር፡፡ በወቅቱ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ለሥራ ያላቸውን ተነሳሽነት በመመልከት በዘርፉ እንዲሠማሩ ድጋፍ አድርገውላቸዋል፡፡ አርሶ አደር መለሰ በዚህ ዓመት ካዘጋጇቸው የፍራፍሬ ችግኞች ከ147 ሽህ በላይ ብር ገቢ አግኝተዋል፡፡
አርሶ አደር መለሰ በ2013/14 የክረምት ወቅት የሚተከሉ ከ47 ሽህ በላይ የፍራፍሬ ችግኞችን አዘጋጅተው ለሽያጭ አቅርበዋል፡፡
አርሶ አደር መለሰ “የተዘጋጁት የፍራፍሬ ችግኞች ከበሽታና ከተባይ ነፃ መኾናቸው በደሴ ኳራንታይን ማዕከል ተረጋግጧል፡፡ አሁን ለመሸጥ ዝግጁ ነኝ” ብለዋል ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ፡፡
በሥራቸው ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የገለጹት አርሶአደሩ ልጆቻቸውንም በአግባቡ እያስተማሩ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ አርሶ አደር መለሰ ልምዳቸውን ለሌሎች በማካፈል እና የሙያ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የቆላ ፍራፍሬ ችግኝ ከማዘጋጀት በተጨማሪ የማንጎ ፍራፍሬ እየሸጡ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
አርሶ አደር መለሰ በእኛ አቅም የወረዳችንን እና የቀበሌአችንን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ አንችልም፤ ሌሎች በዚህ ዘርፍ ቢሠማሩ ውጤት ማስመዝገብ ይችላሉ ብለዋል፡፡
አርሶ አደር ደምል ተሻለ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ የዶገም ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ደምል ከመኸር እርሻ ጎን ለጎን ቡና በማምረት ሥራ ላይ ተሠማርተዋል፡፡ ወደ ሥራው የገቡ በ2004 ዓ.ም ነበር፡፡ የተሻሻለ የቡና ዝርያ በመትከላቸው ችግኙ በተተከለ ከሁለት ዓመት ጀምሮ ምርት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ለቡና ችግኙ የሚጠቀሙበትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በየዓመቱ ያዘጋጃሉ፡፡ ለችግኙ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረጋቸውም በየዓመቱ የተሻለ ምርት ይሰበስባሉ፡፡ አሁን ላይ ሁሉም የቡና ችግኞች ምርት መስጠት በመጀመራቸው ምርታቸው ከስድስት ኩንታል ወደ አስር ኩንታል አድጓል፡፡
በአማራ ክልል በ2013/14 የክረምት ወቅት የሚተከሉ
• 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን የቡና ችግኞች፣
• 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን የቆላ ፍራፍሬ ችግኞች
• 1 ሚሊዮን የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች በመንግሥት እና በግለሰብ ችግኝ ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያው አቶ አወቀ ዘላለም እንዳሉት እስካሁን በ6 ዞኖች ባሉ 21 ወረዳዎች በ148 ቡና አብቃይ ቀበሌዎች በ3 ሽህ ሄክታር መሬት ላይ 5 ሚሊዮን የቡና ችግኝ መትከያ ጎድጓዶች ተዘጋጅተዋል፤ 152 ሽህ በላይ የቡና ችግኞችም ተተክለዋል፡፡ የተዘጋጁ የቆላ ፍራፍሬ ችግኞች በአጭር ጊዜ ምርት የሚሠጡ ናቸው ብለዋል፡፡
የደጋ ፍራፍሬዎችን በ6 ዞኖች በሚገኙ 11 ወረዳዎች ለማሰራጨት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በሥራው ላይ ከ18 ሽህ በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡
በተያዘው የክረምት ወቅት ከ14 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኝ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በዘመናዊ መንገድ እየተዘጋጁ ያሉ የፍራፍሬ ችግኞች የጽድቀት መጠን 95 በመቶ እንደሆነም ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡ ችግኞች የሚታሠበውን ውጤት እንዲሠጡ ከሐምሌ 15/2013 ዓ.ም በፊት መተከል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
የተዘጋጁ ችግኞችን መንግሥት ለአርሶ አደሮች በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚያሠራጭ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ 500 ኩንታል አቮካዶ ለውጭ ገብያ ቀርቧል፤ በቀጣይ ዓመት ሁለት ሽህ ኩንታል አቮካዶ ወደ ውጭ ለመላክ እየተሠራ ነው፡፡ በየችግኝ ጣቢያዎቹ የተዘጋጁ ችግኞች አርሶ አደሮች መንደር ደርሰው ለውጤት እንዲበቁ የሚመለከታቸው የዞን እና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ